ወላጆቿን የገደሉትን የታሊባን ታጣቂዎች የገደለችው ታዳጊ ‘ጀግና’ ተባለች

ታዳጊዋ ኤኬ-47 የጦር መሣሪያ ይዛ የሚያሳየውን ምስል በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተጋሩ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Socila Media

የምስሉ መግለጫ, ታዳጊዋ ኤኬ-47 የጦር መሣሪያ ይዛ የሚያሳየውን ምስል በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተጋሩ ነው።

ባሳለፍነው ሰምንት ወላጆቿን የገደሉትን ሁለት የታሊባን ታጣቂዎችን በጥይት መታ የገደለችው ታዳጊ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ‘ጀግና’ ተብላ እየተወደሰች ነው።

ከ14 እስከ 16 እድሜ መካከል ሳትሆን እንደማትቀር የተገመተችው ታዳጊ፤ በምትኖርበት መንደር የታሊባን ታጣቂዎች ወላጆቿን የገደሉባት ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።

በዚህ የተበሳጨችው ታዳጊ የወላጆቿን ኤኬ-47 ክላሺንኮቨ መሣሪያ ይዛ በመውጣት ሁለት የታሊባን ሚሊሻ አባላትን ስትገድል በርካቶችን ማቁሰሏን የጋሆር ግዛት ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ታጣቂ ሚሊሻዎቹ ታዳጊዋ የምትኖርበት መንደር ድረስ በመምጣት እናት እና አባቷን የገደሉት ወላጅ አባቷ የመንግሥት ደጋፊ ነው በማለት እንደሆነ ባለስልጣናቱ ጨምረው ተናግረዋል።

ታዳጊዋ ኤኬ-47 የጦር መሣሪያ ይዛ የሚያሳየውን ምስል በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተጋሩ ነው።

“ለጀግንነቷ ክብር ይገባታል” ሲል አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ ተናግሯል።

“ወላጆችሽን መልሰሽ እንደማታገኚ እናውቃለን፤ የወሰድሽው የበቀል እርምጃ ግን የህሊና እረፍት ሊሰጥሽ ይችላል” ሲል ሞሐመድ ሳሌህ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ጽፏል።

የአፍጋኒስታን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ፤ በምዕራብ አፍጋኒስታን የምትገኘው ግሆር ግዛት፤ መሠረተ ልማት ካልተስፋፋባቸው የአፍጋን ግዛቶች አንዷ ስትሆን በአካባቢው በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መጠንም ከሌሎች ግዛቶች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

ታሊባን እና የአሜሪካ መንግሥት ከወራት በፊት የሰላም ስምምነት ላይ ደርሰው የነበረ ቢሆንም፤ በርካታ የታሊባን አባላት የአፍጋኒስታን መንግሥት ከስልጣን እንዲወርድ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።