የዩክሬኑ እገታ በፕሬዝደንቱ ያልተለመደ ቪዲዮ ተቋጨ

ዩክሬን

የፎቶው ባለመብት, AFP

በዩክሬን አንድ አጋች ከ10 በላይ የሚሆኑ ሰዎቸን በአውቶብስ ላይ አግቶ መቆየቱ ይታወሳል።

በከፍተኛ ደረጃ የታጠቀው ሩሲያዊው አጋች ወደ ፖሊስ ሁለት ጊዜ ከመተኮሱም ባለፈ የእጅ ቦምብ ወደ ፖሊስ ወርውሮ ነበር።

ይሁን እንጂ የዩክሬን ፕሬዝደንት በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው በአጋቹ ጥያቄ ሠረት ያልተለመደ ይዘት ያለው ተንቀሳቃሽ ምስል የፌስቡክ ገጻቸው ላይ ከለጠፉ በኋላ ፖሊስ 10 ታጋቾችን ነጻ አውጥቶ አጋቹን በቁጥጥር ሥር አውሏል።

የዩክሬን መገናኛ ብዙሃን ከእገታው በኋላ አጋቹ እጁ ወደኋላ ተጠርንፎ እና መሬት ላይ በደረቱ ተንጋሎ አሳይተዋል።

አጋቹ ከመያዙ በፊት ፕሬዝደንት ቮሎደይመር ዜሌኔስኪ በአጋቹ ጥያቄ መሠረት፤ “ሁሉም ሰው 2005 ላይ የተሠራውን 'ኤርዝሊንግ' የተሰኘውን ፊልም መመልከት አለበት” የሚል ቪዲዮ ለጥፈው ነበር።

አጋቹ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ፕሬዝደንት ዜሌኒስኪ ተንቀሳቃሽ ምስሉን ከገጻቸው ላይ አጥፍተውታል።

በሆሊውድ የተሠራው ይህ ፊልም የእንስሳት መብት ላይ የሚያጠነጥን ዘጋቢ ፊልም ነው።

በዘጋቢ ፊልሙ ግዙፍ የዓለማችን ኢንደስትሪዎች የንግድ እንቅስቃሴያቸውን ለማስቀጠል ምን ያህል እንስሳት ላይ እንደሚመረኮዙ ያሳያል።

አጋቹ የሩሲያ ዜጋ የ44 ዓመት ጎልማሳ ማከሰይም ክራይቮሽ እንደሆነ የዩክሬን ፖሊስ ይፋ አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, አጋቹ የሩሲያ ዜጋ የ44 ዓመት ጎልማሳ ማከሰይም ክራይቮሽ እንደሆነ የዩክሬን ፖሊስ ይፋ አድርጓል።

አጋቹ የሩሲያ ዜጋ የ44 ዓመት ጎልማሳ ማከሰይም ክራይቮሽ እንደሚባል እና ከዚህ ቀደም በወንጀል ድርጊቶች የተፈረደበትበን አጠናቆ ከእስር የወጣ ስለመሆኑ፤ እንዲሁም የአእምሮ ጤና ችግር አጋጥሞት የህክምና ድጋፍ ሲደረግለት እንደነበረ ተነግሯል።

በምሥራቅ ዩክሬን በምትገኘው ሉተስክ ከተማ 20 ሰዎችን አግቶ ይዞ የነበረው ሩሲያዊ፤ ተቀጣጣይ ነገሮችን ታጥቆ እንደሚገኝ በማሳወቅ እውቅ ፖለቲከኞች እራሳቸውን "ሽብርተኛ ነን" ብለው እንዲጠሩ ጠይቆ እንደነበረ ቀደም ሲል ፖሊስ አስታውቋል።

በጠቅላላው ታግተው የነበሩት 13 ሰዎችን ከበርካታ ሰዓታት በኋላ ምንም አይነት አካላዊ ጉዳት ሳይደርስባቸው ከእገታው ነጻ ወጥተዋል።