አንድ ሩሲያዊ ታጣቂ 20 ሰዎችን አውቶብስ ላይ አግቶ ከፖሊስ ጋር ተፋጧል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዩክሬን ፖሊስ 20 ሰዎችን አውቶብስ ላይ አግቶ ከያዘው ሩሲያዊ ጋር ተፋጦ እንደሚገኝ ተነገረ።
ሩሲያዊው አጋች በከፍተኛ ደረጃ የታጠቀ ሳይሆን እንደማይቀር የተገመተ ሲሆን፤ አጋቹ ወደ ፖሊስ ሁለት ጊዜ መተኮሱን እና የእጅ ቦምብ ወርውሮ እንደነበረ ፖሊስ አስታውቋል። አጋቹ የወረወረው የእጅ ቦምብ እንዳልፈነዳ ተነግሯል።
"አጋቹ ከአውቶብሱ ውስጥ ሆኖ ቦምብ ወርውሮ ነበር። መልካም አጋጣሚ ሆኖ ቦምቡ ሳይፈነዳ ቀርቷል" ይላል ፖሊስ ያወጣው መግለጫ።
አጋቹ የሩሲያ ዜጋ የ44 ዓመት ጎልማሳ ማከሰይም ክራይቮሽ እንደሚባል እና ከዚህ ቀደም በወንጀል ድርጊቶች የተፈረደበትበን አጠናቆ ከእስር የወጣ ስለመሆኑ፤ እንዲሁም የአእምሮ ጤና ችግር አጋጥሞት የህክምና ድጋፍ ሲደረግለት እንደነበረ ተነግሯል።
ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በማጭበርበር እና ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ በመያዝ በሚል የወንጀል ድርጊቶች 10 ዓመታትን በእስር አሳልፏል።
በምሥራቅ ዩክሬን በምትገኘው ሉተስክ ከተማ 20 ሰዎችን አግቶ የያዘው ሩሲያዊ፤ ተቀጣጣይ ነገሮችን ታጥቆ እንደሚገኝ በማሳወቅ እውቅ ፖለቲከኞች እራሳቸውን "ሽብርተኛ ነን" ብለው እንዲጠሩ እየጠየቀ ስለመሆኑ ፖሊስ አስታውቋል።
የአገሪቱ አቃቤ ሕግ በበኩሉ አጋቹ በከተማዋ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች በርቀት መፈንዳት የሚችሉ ቦምብ አጥምዶ እንደሚገኝ መናገሩን አስታውቋል።
የዩክሬን የአገር ውስጥ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር አንቶን ሄራቼንኮ፤ ፖሊስ ጉዳዩን በድርድር ለመፍታት ካለው ፍላጎት የመነጨ አጋቹን ለማነጋገር ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
በአውቶብሱ ላይ ለበርካታ ሰዓታት ታግተው የሚገኙት የታጋቾች ሁኔታ ምን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።
ፖሊስ የከተማዋ ነዋሪዎች በያሉበት እንዲቆዩ፤ ከቤት እና ከቢሯቸው እንዳይወጡ ጠይቋል።
የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎደሜይር ዜሌኒስኪ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ እንደሆነም ተናግረዋል።












