በሁከቱ ከ1ሺህ በላይ መኖሪያና ንግድ ቤቶች፣ ከ240 በላይ ተሽከርካሪዎች ወድመዋል

የፎቶው ባለመብት, -
ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ከተሰማ በኋላ በኦሮሚያ ክልል ከ1 ሺህ በላይ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት መድረሱ ተነገረ።
የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ለቢቢሲ አንደተናገሩት፤ መንግሥት በመኖሪያ ቤቶች፣ በንግድ ቤቶች እና በመንግሥት ተቋማት ላይ የደረሱትን ጉዳቶች፤ "የተቃጠሉ፣ የተሰባበሩ እና የተዘረፉ" በሚሉ ጎራዎች ከፋፍለው የደረሰውን የጉዳት እያጠኑ መሆኑን አስረድተዋል።
ቃል አቀባዩ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋገት በቤቶች ላይ የደረሰው ጉዳት የሚከተለው ነው።
በመኖሪያ እና በንግድ ቤቶች ላይ የደረሰ ጉዳት
የአርቲስቱ ግድያ ከተሰማ በኋላ በአሮሚያ ክልል፤ 523 መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል። 499 መኖሪያ ቤቶች ደግሞ እንደተሰባበሩ የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው በንግድ ቤቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት በአሃዝ ሲያስቀምጡ፤ 195 ሆቴሎች መቃጠላቸውን እና ሌሎች 32 ሆቴሎች ደግሞ በንብረት ላይ የመሰባበር ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም 104 የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የቃጠሎ ውድመት እንደደረሰባቸው አመልክተዋል።
ስድስት አነስተኛ እና ግዙፍ ፋብሪካዎች በሁከቱ መቃጠላቸውን የተናገሩት አቶ ጌታቸው፤ የተቃጠሉ አነስተኛ ንግድ ቤቶች ቁጥር ድግሞ 232 እንዲሁም የተሰባበሩት አስተኛ ንግድ ቤቶች አሃዝ 219 መሆኑን አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, -
በተሽከርካሪዎች ላይ የደረሰ ጉዳት
የክልሉ ቃል አቀባይ እንደሚሉት ከሆነ 232 የግል እንዲሁም 12 የመንግሥት ተሸከርካሪዎች በእሳት እንዲጋዩ ተደርገዋል።
በአጠቃላይ በግል እና በመንግሥት ቤቶች እንዲሁም ተሽከርካሪዎች ላይ የደረሰው ጉዳት መጠን እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል። ዘረፋን በተመለከተ ግን የተሰባሰቡ ማስረጃዎች ተጠናቅረው ስላላለቁ ዝርፊያ የተፈጸመበትን የንብረት መጠን ማወቅ ለጊዜው አዳጋች እንደሆነ ተናግረዋል።
'ጉዳቱ የደረሰው በሁሉም ላይ ነው'
በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰው በምዕራብ አርሲ ሦስት ወራዳዎች ውስጥ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጌታቸው፤ በተለይ በሻሸመኔ እና ባቱ ከተሞች እንዲሁም በባሌ ዞን ሮቤ እና አጋርፋ ከተሞች የደረሰው ገዳት ከሌሎች አካባቢዎች አንጻር ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ ህይወታቸውን ያጡት፣ ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው ሰዎች የአንድ ብሔር ወይም ሐይማኖት ተከታይ አይደሉም ብለዋል። "በአንደ ብሔር እና ሐይማኖት ላይ ብቻ ያነጣጠረ አልነበረም። ሁሉም ብሔር እና የሐይማኖት ተከታዮች ጉዳት ደርሶባቸዋል" ሲሉ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
መልሶ ማቋቋም
ቤት ንብረታቸው ተቃጥሎባቸው ባዶ እጃቸውን ቀርተው የእምነት ተቋማትን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች ቁጥር በርካታ መሆኑን አቶ ጌታቸው ገልጸው፤ በተፈጸመው ውድመት ንብረታቸው ወድሞባቸው የመንግሥት እርዳታን የሚሹ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺህ በላይ እንደሚሆን አመልክተዋል።
ንብረታቸው የወደመባቸው ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። "የምግብ እና የአልባሳት ድጋፍ በያሉበት እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው" ሲሉ አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ቁጥር
ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በተፈጠረው አለመረጋጋት በኦሮሚያ ክልል በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰዎች ቁጥር 7123 መድረሱን አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የክልሉ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ጨምረውም በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሰዎች ጋር በተያያዘ ፖሊስ አና አቃቢ ሕግ ከ5 ሺህ በላይ በሚሆኑ መዝገቦች ተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ መመስረታቸውንም አመልክተዋል።
አቶ ጌታቸው "መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ጠንክሮ እየሰራ ነው" ካሉ በኋላ፤ "በጸጥታ ኃይሎች የተያዙ ሰዎችም በቁጥጥር ከዋሉበት በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የማቅረብ ሥራ እየተሰራ" መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ ባሻገር ከሁከቱ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙና በተባለው የጊዜ ገደብ ውስጥ ፍርድ ቤት አልቀረቡም ስለሚባሉ ሰዎች በተመለከተ "እስካሁን ተይዘው ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሰዎች ስለመኖራቸው መረጃው የለኝም" ብለዋል።















