የታሰሩ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ መንግሥት እንዲያሳውቅ አምነስቲ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአገሪቱ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በቁጥጥር ስር የዋሉ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ እንዲያሳውቅ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግሥትን ጠየቀ።
በአዲስ አበባ ከተማና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ቢያንስ 5 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቀሰው አምነስቲ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የት እንዳሉ በማይታወቁበት ሁኔታ ተለይተው መያዛቸውን አመልክቷል።
ጨምሮም በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ጃዋር መሐመድን ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ፣ እሰክንድር ነጋ ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ እና ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ዋነኛ የተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት ተገልጿል።
ባለስልጣንት ታሳሪዎቹ ያሉበትን ቦታ ለቤተሰቦቻቸው ባለማሳወቃቸው ጭንቀትን እየፈጠሩ መሆናቸውን በመጥቀስ "በአስቸኳይ ያሉበትን ቦታ በማሳወቅ ክስ እንዲመሰርቱባቸው ካልሆነም በአስቸኳይ እንዲለቀቁ" ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ ኃላፊ ዲፕሮስ ሙቼና ጠይቀዋል።
መግለጫው ጨምሮም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አሳሳቢ በሆነበት በዚህ ወቅት ንጽህናቸው ባልተጠበቁና በተጨናነቁ ሁኔታዎች ውስጥ ሊታሰሩ ይችላሉ በሚል የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ጭንቀት ውስጥ ናቸው ብሏል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ዋነኛ ባለስልጣናት የት እንዳሉ ለማወቅ እንዳልቻሉ ጠበቆቻቸው እንደተናገሩ የጠቀሰው ሪፖርቱ የፌደራል፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖችን ጨምሮ ግለሰቦቹ በእነሱ ቁጥጥር ስር እንዳልሆኑ እንደገለጹላቸው አመልክተዋል።
"ግለሰቦችን በእስር ለማቆየት የሚቻለው ፖሊስ በታሳሪዎቹ ላይ ጠንካራ ማስረጃ ካለው ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ፖሊስ ማስረጃ በሚያፈላልግበት ጊዜ ሰዎች የነጻነት መብታቸው ተገፎ ሊታሰሩ አይገባም" ብለዋል ዲፕሮስ ሙቼና።
አምነስቲ በሪፖርቱ ላይ በእስር ላይ ይገኛሉ ያለቸውን ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን ጠቅሶ በማስረጃ ክስ እንዲመሰረትባቸው አሊያም እንዲለቀቁ ጠይቋል። አክሎም "የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ወደተለመደው የጭቆና መንገድ መመለስ የለባቸውም። የመቃወምና የተለየ የፖለቲካ ሃሳብ ማራመድን መብት ማክበር ይጠበቅባቸዋል" ሲሉ የድርጅቱ የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ ኃላፊ ማሳሰባቸውን ገልጿል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በተከሰተው አለመረጋጋት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ወደ የማኅበረሰባዊ ጥቃት በተሸጋገሩ ተቃውሞዎችና በጸጥታ ኃይሎች ቢያንስ 177 ሰዎች መገደላቸውንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መቁሰላቸውን በሪፖርቱ አመልክቷል።
















