የሃጫሉ ግድያ፡ ከሁከቱ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች ወደ 5 ሺህ ተጠግቷል ተባለ

አቶ ንጉሱ ጥላሁን

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

ባለፈው ሰሞን ተከስቶ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 5 ሺህ እንደሚጠጋ የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለቢቢሲ ተናገሩ።

አቶ ንጉሡ በአሁኑ ጊዜ የአገሪቱ የጸጥታ ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑን ጠቁመው፤ ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ተከስቶ በነበረው ሁከት በሰው እና በንብረት ላይ ከደረሰው ጉዳት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር 5 ሺህ ገደማ እንደሆነ ገልጸዋል።

ክስተቱን ተከትሎ "የጸጥታ መዋቅሩ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ ነው" ያሉት አቶ ንጉሡ፤ አሁንም በጸጥታ አካሉ እየተፈለጉ ያሉ ሰዎች መኖራቸውን አመልከተዋል።

አቶ ንጉሡ ጨምረው እንደተናገረት ተከስቶ በነበረው ሁከት በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ከፌደራል እና ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተወጣጣ አካል አለመረጋጋቱ አጋጥሞባቸው ወደነበሩት ስፍራዎች ማምራቱን ተናግረዋል።

የደረሰውን ጉዳት በሚመለከትም ግብረ ኃይሉ የሚያጠናቅረው ዝርዝር መረጃ ዝግጁ ሲሆን ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ የመንግሥት ባለስልጣናት እስር

ከሃጫሉ ግድያ በኋላ የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ የመንግሥት ባለስልጣናት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን ያረጋገጡት አቶ ንጉሡ፤ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ "ሁሉም አይነት አመራር ይኖራል። የሚልቀው ብጥብጡ እና ቀውሱን ለመቆጣጠር የሚታገል ነው" በማለት አብዛኛው አካል አውንታዊ ጥረት ማደረጉን አመልክተዋል።

"ከዚህ ውጪ ሁለት ቦታ የሚረግጥ ይኖራል፣ የተሳሳተ ይኖራል አልያም ደግሞ የብቃት ችግር ያለበት ይኖራል" ያሉ ሲሆን፤ ሁሉም እንደ አግባቡ "በሕግ የሚጠየቀው በሕግ ይጠየቃል፣ ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚያስፈልገው ፖለቲካዊ ውሳኔ ይተላለፍበታል እንዲሁም አስተዳደራዊ እርምጃ የሚሰጣቸውም ይኖራሉ" ብለዋል።

ችግር የፈጠሩ፣ ያባባሱና አይተው እንዳለየዩ ያለፉ አመራሮች እንዲሁም የጸጥታ አስከባሪ አካላት መኖራቸውን ጠቁመው በጉዳዩ ላይ በቀጣይ የማጣራት ሥራ እንደሚሰራ አቶ ንጉሡ ተናግረዋል።

የጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች እስር

"በሚዲያው በሚረጨው መርዝ ዜጎች ህይወታቸው የሚቀጠፍበትና ኢትዮጵያ የምትፈርስበት እድል ሊፈቀድ አይደገባም" ያሉት አቶ ንጉሡ፤ "የሚኖሩበትን ሕዝብና አገር እያጫረሱ እንዲፈርስ እየጣሩ የሚዲያ ተቋም ነን ሊሉ አይችሉም፤ ጋዜጠኛ ነን ሊሉም አይችሉም" ያሉ ሲሆን መሰል ግለሰቦች ላይ "ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል" ብለዋል።

የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ

ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግንድያ በኋላ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ መንግሥት በመላው አገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል። ይህንንም በተመለከተ የኢንትኔት አገልግሎት ወደ ነበረበት የሚመለስበትን ጊዜ ቢቢሲ አቶ ንጉሡን ጥይቆ ነበር።

"ኢንተርኔት የተዘጋው ለጸጥታ ሲባል ነው" ያሉት አቶ ንጉሡ፤ ጨምረውም የአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ሲረጋገጥ ሙሉ የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሚለቀቅ ተናግረዋል።

አቶ ንጉሱ ጨምረውም "አሁንም ቢሆን ሕዝቡ 'ፌስቡክ የሚባለውን ያዝ አድርጉልን። በብሔርና በሐይማኖት ላይ የክተት ጥሪ እየተጠራ ነው' የሚሉ አስተያየት እየሰጡን ነው" በማለት በሕዝቡ ዘንድ ከኢንተርኔት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ስጋት እንዳለ እንደሚገነዘቡ ጠቅሰዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከማክሰኞ ከሰዓት ኋላ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በከፊል የኢንተርኔት አገልግሎት ክፍት መደረጉን ቢቢሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዚህም መሰረት ከአዲስ አበባ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በተለያዩ ቦታዎች ላይ የዋይፋይ ኢንተርኔት አገልግሎት ክፍት ቢደረግም በርካቶች የሚጠቀሙት የሞባይል ዳታ የኢንተርኔት አገልግሎት ግን አሁንም እንደተዘጋ ነው።