ከሃጫሉ ግድያ ጋር ተያይዞ አቃቤ ሕግ እስካሁን ያነሳቸው አራት ቁልፍ ነጥቦች

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ

የዛሬ ሁለት ሳምንት ሰኔ 22/2012 ዓ.ም ምሽት 3፡30 ገዳማ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ አዲስ አበባ ውስጥ በጥይት ተመትቶ መገደሉ ይታወሳል።

ከሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ፖሊስ የተወሰኑ ተጠርጣሪዎችን መያዙን አስታውቆ በተከታታይ በነበሩት ቀናትም ተጨማሪ ሰዎች ከወንጀሉ ጋር በተገናኘ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ በተለይ በግድያው ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ ፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በተለይ ባለፈው ሳምንት ተከታታይ መረጃዎች ሰትቷል።

"ሃጫሉን ተኩሶ የገደለው ጥላሁን ያሚ ነው"

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሐምሌ 3/2012 ዓ.ም በሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በቀጥታ ተሳትፈዋል ያላቸውን የሦስት ግለሰቦችን ማንነት ይፋ አድርጓል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በሰጡጥ መግለጫ በድምጻዊ ሃጫሉ ግድያ በቀጥታ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩትን ጥላሁን ያሚ፣ አብዲ አለማየሁ እና ከበደ ገመቹ (በወቅቱ በቁጥጥር ሥር አልዋለም ነበር) መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ሃጫሉ ሁንዴሳን ተኩሶ የገደለው ጥላሁን ያሚ አንደሆነም በዕለቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ ተጠርጣሪው የሰጠውን ቃል ጠቅሰው ይፋ አድርገዋል።

መግለጫው ከተሰጠ ከሰዓታት በኋላም ሦስተኛው ተጠርጣሪ ከበደ ገመቹ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ አደአ ውስጥ ድሬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ዐቃቤ ሕግ አስታወቋል።

ተጠርጣሪዎች "ተልዕኮ የተቀበሉት ከኦነግ-ሸኔ ነው"

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንዳሉት ተጠርጣሪዎቹ የግድያውን ተልዕኮ ኦነግ-ሸኔ ከተባለው ቡድን ተቀብለው ማስፈጸማቸውን በመግለጽ፤ ቡድኑ ከግድያው ጀርባ እጁ እንዳለበት ተናግረዋል።

ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ተኩሶ የገደለው ጥላሁን ያሚ የተባለው ግለሰብ ተልዕኮውን ከኦነግ-ሸኔ እንደተቀበለና ድምጻዊውን ኢላማ ማድረግ ለምን እንዳስፈልገ በሰጠው ቃል መግለጹንም ተናግረዋል።

የግድያ ተልዕኮውን እንዲፈጽም ከሸኔ ቡድን በሰኔ ወር ውስጥ ሦስት ጊዜ መገናኘቱንም አሳውቀዋል።

"ሃጫሉ ተደጋጋሚ ማስፈራሪያዎች ይደርሱት ነበር"

ከሁለት ቀናት በፊት ማለትም ቅዳሜ ሐምሌ 4 ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የፌደራል ፖሊስ በሰጡት የጋራ መግለጫ ለይ ሃጫሉ ተደጋጋሚ የግድያ ማስፈራሪያዎች ይደርሱት እንደነበረ አስታውቀዋል።

በመግለጫው በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ጸጋ፤ በሃጫሉ ሁንዴሳ የእጅ ሰልክ ላይ ተደጋጋሚ የግድያ ዛቻዎች ይደርሱት እንደነበረ አመልከተዋል። አቶ ፍቃዱ ጨምረውም ሃጫሉ ለጓደኞቹ ዛቻዎች እየተሰነዘሩበት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገር እንደነበረ አስታውቀዋል።

በቴሌግራም አማካንኝነት ደግሞ እራሱን የኦነግ-ሸኔ አስተባባሪ ከሚል ግለሰብ በድምጽ እና በጽሑፍ ማስፈራሪያዎች ሲደርሱት እንደነበረም አቶ ፍቃዱ ጨምረው አስረድተዋል።

"ኦኤምኤን የሃጫሉን ቃለ መጠይቅ ቆርጦ አስተላልፏል"

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ከመገደሉ ከአንድ ሳምንት በፊት ከኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦኤምኤን) ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ አየር ላይ መዋሉ ይታወሳል።

አቶ ፍቃዱ እንዳሉት ከሆነ ኦኤምኤን አርቲስቱ በቃለ መጠይቁ ከኦነግ-ሸኔ የግድያ ዛቻ በተደጋጋሚ እንደሚደርሰው የተናገረበትን የቃለ መጠይቅ ክፍል ተቆርጦ እንዲወጣ ተደርጓል።

ሃጫሉ በቃለ መጠይቁ ላይ ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር እንዲጋጭ የሚያደርጉ ሌሎች አመለካከቶቹን እንዲያጸባርቅ በጠያቂው በኩል ተደርጓልም ብለዋል አቶ ፍቃዱ።

አቶ ፍቃዱ እንዳሉት አርቲስት ሃጫሉ ከኦኤምኤን ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ 1 ሰዓት ከ 11 ደቂቃ እንደሚረዝም ተናግረው በኦኤምኤን የተላለፈው ግን 47 ደቂቃ በቻ ነው ብለዋል። ተቆርጦ እንዲቀር የተደረገው ክፍልም ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

ተቆርጦ እንዲቀር የተደረገው ከኦነግ-ሸኔ ይደርስበት የነበረው ዛቻ ብቻ ሳይሆን፤ "በዚህ አገር ለውጥ መምጣቱን፣ ይሄ ለውጥ እያደገ ሊሄድ እንደሚችል፣ ለውጡን መደገፍ አማራጭ የሌላው ነገር መሆኑን፣ አብሮ መቆም የሚያስፈልግ መሆኑን . . ደጋግሞ የሚያሰቀምጥባቸው ቦታዎች ናቸው ተቆርጠው እንዲቀሩ የተደረጉት" ሲሉ አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል።

ሃጫሉ ከዚህ ቀደም ምን ብሎ ነበር?

ሃጫሉ ሁንዴሳ ከዚህ ቀደም ቢቢሲን ጨምሮ ከሌሎች መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ተደጋጋሚ የግድያ ዛቻዎች ይደርሰው እንደነበረ ተናግሯል።

ከግድያው ከሳምንት በፊት ሰኔ 15/2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ላይ በተላለፈው ቃለ መጠይቁ፤ ሃጫሉ "እየታገልኩ እኮ ነው የምኖረው" በማለት ተደጋጋሚ የግድያ ዛቻ እንደሚደርስበት ተናግሮ ነበር።