ከሃጫሉ ግድያ በኋላ ያለፉት ሁለት ቀናትና የዛሬ የአዲስ አበባ ውሎ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከሰሞኑ ገላን አካባቢ በመኪናው ውስጥ የተገደለው ድምፃዊና የፖለቲካ አቀንቃኙ የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በርካቶችን አስደንግጧል፤ እንዲሁም በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎችም ተቃውሞዎች እንዲቀጣጠሉ ምክንያት ሆኗል።
ለአርቲስቱ ወዳጆችና አድናቂዎች እንዲህ ህይወቱ በአጭር መቀጠፉም ሆነ በኦሮሞ ትግል ውስጥ 'ነፀብራቅ' የሚሉት ድምፃዊ መቀጨት ብዙዎች አልተዋጠላቸውም።
በሙዚቀኛው ሞት ማግስት በተለያዩ አዲስ አበባ አካባቢዎች መፈክሮችንና ሽለላዎችን እያሰሙ እንዲሁም ቁጣቸውን የሚገልፁ ወጣቶች ተስተውለዋል። ሃጫሉ በተገደለበት ገላን አካባቢም የተቃጠሉ የመኪና ጎማዎች ጎዳናውን ሞልተውት እንዲሁም አጥቁረውት ነበር። የተለያዩ ህንፃ መስታወቶች መሰባበር፣ ዘረፋና የንብረት መውደምም አጋጥሟል።
ከፍተኛ የጥይት ድምፆች እንዲሁም ቆንጨራና ዱላ የያዙ በቡድን የተከፋፈሉ ወጣቶች በየጎዳናው መታየታቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል።
በዚያኑ ቀንም ነው በአዲስ አበባ ሦስት የቦምብ ፍንዳታዎች ተከስተው ቁጥራቸው ያልተገለፁ ሰዎችም ህይወት መጥፋቱን እንዲሁም በርካቶችም መቁሰላቸው በፖሊስ የተነገረው።
ቦምቡን ያፈነዱት መሞታቸውን፣ እንዲሁም የቆሰሉና የሌሎችም ዜጎች ህይወት ቢጠፋም ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ የፌደራል ፖሊስ አልጠቀሰም ነበር።
በትናንትናው ዕለት ጥዋት ሁኔታዎች የተረጋጉ ቢመስሉም ከሰዓት በኋላ የተኩስ ድምፅ ከተለያየ አካባቢ ይሰማ እንደነበርም ቢቢሲ መረዳት ችሏል። በአዲሱ ገበያ፣ ላም በረት፣ ሲኤምሲና ሰሚት የካ አባዶና ሌሎች አካባቢዎች በብዛት ሰብሰብ ብለው እየጨፈሩ የነበሩ ወጣቶችም ተስተውለዋል።
በተለይም አዲስ አበባ ምሥራቃዊ ክፍል በሚገኙት ካራ፣ የካ አባዶና አያት አካባቢዎች ከማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ውጥረትና ፍርሃት ነግሶ ቆይቷል።
የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ከሌላ አካባቢ በቡድን ሆነው ዱላና ብረት በመያዝ የመጡ ወጣቶች ናቸው ያሏቸው የመኪኖችን፣ የመኖሪያ ቤቶችንና ህንጻዎችን መስታወቶች በመስበር ጉዳት እንዳደረሱ ገልጸው፤ ሱቆች ላይ የዘረፋ ሙከራ ተደርጎ እንደነበርም ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በተለይ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ድርጊቱ መደጋገሙንና የወጣቶቹም ቁጥር ብዙ እንደነበር ገልጸው፤ ከነዋሪው ጋር ግጭት ውስጥ ተገብቶ ከባድ ችግር ይፈጠራል የሚል ስጋት እንደነበር ገልጸዋል። ነገር ግን አመሻሽ ላይ የጸጥታ ኃይሎች በብዛት በመሰማራታቸው ወጣቶቹ ወደ መጡበት ተመልሰዋል ብለዋል።
በትናንትናው ዕለትም እንዲሁ ስጋትና አለመረጋጋቱ በተለያዩ ሰፈሮች የነበረ ሲሆን ሰሚት አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ከበራቸው ላይ ሆነው ሌሊቱን ሲጠብቁ እንደነበር አስረድተዋል።
በተለይም ፍየል ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባሉ አፓርትመንቶች (የጋራ መኖሪያ ቤቶች) ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንዳስረዱት ምሽቱ ፍርሃት የነገሰበት እንደነበርና አንድ የንግድ ተቋምም ለመዝረፍ መሞከሩንም እንዲሁ አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በርካታ የፀጥታ አስከባሪዎችም በአካባቢው እንደተሰማሩም ገልፀዋል። በፈረንሳይ፣ ስድስት ኪሎ፣ ፒያሳና እንዲሁም በሌሎች ሰፈሮች ተኩስ መስማታቸውንም የተለያዩ ነዋሪዎች ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ሃያ ሁለት ዘሪሁን ሕንጻ አካባቢ ትናንት ቀን ስምንት ሰዓት ላይ ተኩስ እንደነበር እና ከሌላ አካባቢ መጡ ያሏቸው ሰዎች ሊረብሹ መሞከራቸውን የተናገሩት አንድ ነዋሪ በዚህም የተነሳ ዛሬ ከቤታቸው ሳይወጡ መዋላቸው ይናገራሉ።
እንዲሁ ኮተቤ አካባቢ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ ተኩስ ይሰማ እንደነበር የተናገሩት ሌላ ነዋሪ ደግሞ ለሊቱ ሰላማዊ እንደነበር ተናግረዋል።
ነገር ግን ወሰን አካባቢ በነበረ የመንገድ መዝጋትና ጎማ ማቃጠል የተነሳ ከቤታቸው ርቆ ለመንቀሳቀስ ፍርሃት እንዳለባቸው አልሸሸጉም።
አያት አካባቢ የሚገኙ ኮንዶሚኒየሞች እና የአየር መንገድ ማኅበር ቤቶች አካባቢ ግን ምሽት በቡድን የመጡ ሰዎች ነዋሪዎችን ሰላም ነስተው እንደነበር ገልፀው የአካባቢው ነዋሪ በጋራ ለመከላከል መውጣቱን እንዲሁም የተወሰኑትን ለፖሊስ ማስያዙን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአየር መንገድ ማኅበር ቤቶች ውስጥ ግቢውን ሰብረው የገቡ ወጣቶች ረብሻ ለማስነሳትና ንብረት ለማውደም ቢሞክሩም ነዋሪዎች በጋራ መከላከላቸውንና በአሁኑ ሰዓትም በግቢያቸው ውስጥ የፖሊስ ኃይሎች እንደሚገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ወደ መገናኛ በአንድ ቢሮ ውስጥ ለሚሰሩ ግለሰብ ደውሎ ያለውን ሁኔታ ለማጣራት ሙከራ ያደረገ ሲሆን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ደካማ መሆኑን ነገር ግን መንገዱ ሰላማዊ እንደነበር ለመረዳት ችሏል።
ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ምንም አይነት ግጭት ባይስተዋልም በአብዛኛው የከተማዋ ከፍል ፍርሃት እንዳንዣበበ መሆኑንም ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል። አዲስ አበባ ጭር ያለች ሆናለች፤ የተለመደው የወትሮው እንቅስቃሴም የማይታይባት ከተማም ሆናለች።
በተለይም ትናንትና ይሰማ የነበረው ተኩስና ከአንዳንድ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ከባድ ፍርሃት መፍጠሩንና ዛሬም ከቤት ሳይወጡ እንዳረፈዱም የተናገሩ በርካቶች ናቸው።
ከአንዳንድ ውር ውር ከሚሉ ታክሲዎች በስተቀር ትራንስፖርትም አለመኖሩን እንዲሁም የንግድ እንቅስቃሴዎችም ቀጥ ማለታቸውን ተናግረዋል። ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶች እንደተዘጉ ናቸው።
የከተማው ፖሊስና የፌደራል ፖሊስ በርከት ብለው መታየታቸውን ቢቢሲ በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች አይቷል። ከዚህም በተጨማሪ ሲኤምሲ፣ ሃያ ሁለት፣ ቦሌ አካባቢዎች የመከላከያ ሠራዊት አባላት በፒክ አፕ ተጭነው የፀጥታ ሁኔታውን እየተቆጣጠሩ ነው።
በከተማይቱ ውስጥ ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት የስምንት ነዋሪዎችና የሁለት ጸጥታ አስከባሪዎች ህይወት ማለፉንም የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል።
ትናንት ምሽት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እንዳሉት ማክሰኞና ረቡዕ ስምንት የከተማዋ ነዋሪዎች ህይወት ማለፉን ገልጸዋል። እነዚህ ግለሰቦች የሞቱት "በቦምብ፣ ጥይት፣ በድንጋይ እና በመሳሰሉት ነው" ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በነበረው አለመረጋጋትም የግል እና የመንግሥት ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል፤ ተሰባብረዋል። "የዜጎችን ያፈሩትን ሃብት እና ንብረት የመዝረፍ እንቅስቃሴ ነበር" በማለትም አስረድተዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ መግለጫ ንብረትነታቸው የግለሰብ እና የመንግሥት የሆኑ 250 ተሽከርካሪዎች ተሰባብረዋል፣ 20 ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል።












