በአዲስ አበባ ባለፉት ሁለት ቀናት ሁለት ፖሊሶችን ጨምሮ የ10 ሰዎች ህይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, ETV
በአዲስ አበባ ውስጥ ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት የስምንት ነዋሪዎችና የሁለት ጸጥታ አስከባሪዎች ህይወት ማለፉን የከተማዋ ፖሊስ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ በብሔራዊው ቴሌቪዥን ቀርበው እንደተናገሩት ከማክሰኞ ጀምሮ በመዲናዋ የጸጥታ መደፍረስ እንዳጋጠመ አስታውቀዋል።
ኮሚሽነር ጌቱ በከተማዋ ውስጥ በዜጎች ላይ ደረሰ ባሉት ጉዳት "ማክሰኞና ረቡዕ የ8 ሰዎች ህይወት አልፏል" ካሉ በኋላም፣ ነዋሪዎች ህይወታቸው ያለፈው "በቦምብ፣ ጥይት፣ በድንጋይ እና በመሳሰሉት ነው" ብለዋል።
የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ተሰማርተው የነበሩ የፖሊስ አባላት ላይ ከቀላል የአካል ጉዳት እስከ ሞት የደረሰ ጉዳት መድረሱንም ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ ጨምረውም "ማክሰኞ እና ረቡዕ 57 የሚሆኑ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት ደርሷል" በማለት ሁለት የፖሊስ አባላት ደግሞ ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።
በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች በነበረው አለመረጋጋትም "የግል እና የመንግሥት ተሽከርካሪዎችን መሰባበር እና ማቃጠል፣ የዜጎችን ያፈሩትን ሃብት እና ንብረት የመዝረፍ እንቅስቃሴ ነበር" ኮሚሽነሩ ጌቱ አርጋው።
ንብረትነታቸው የግለሰብ እና የመንግሥት የሆኑ 250 ተሽከርካሪዎች ተሰባብረዋል፣ 20 ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል ሲሉም አክለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ትናንት ምሽት በሰጠው መግለጫ ላይ ጨምሮ እንዳለው አብን እና ባልደራስ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የብሔር ግጭት ለመቀስቀስ ሞክረዋል ብሏል።
በዚህም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት መሳተፋቸውን ገልጸው በተለይ የባልደራስ እና አብን አመራሮች እና አባላት በግልጽ ቲሸርት በመልበስ እና የፓርቲያቸውን አርማ በመያዝ፤ በከተማዋ የተለያየ አካባቢዎች እተንቀሳቀሱ "የብሔር ግጭት ለመፈጥር እንቅስቃሴ ሲደረጉ ነበር" ብለዋል።
"በተለያዩ የከተማው አቅጣጫ በመንቀሳቀስ አንዱ ብሔር ሌላውን ሊያጠቃ እንደመጣ፤ እየተወረረ እንደሆነ" በመግለጽ "እንዲከላከል" ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነበር ብለዋል።
ጨምረውም ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በከተማዋ ሁከት እና ብጥብጥ በመፍጠር ኅብረተሰቡ እርስ በእርሱ እንዲጋጭ እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ እንደነበር አመልክተዋል።












