"በሦስቱ ሰኔዎች ጉዟችንን የማደናቀፍና ደም የማፍሰስ ሙከራዎች ተደርገዋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

የፎቶው ባለመብት, ETV

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ማምሻውን በአገሪቱ የቴሌቭዢን ጣብያ ላይ ቀርበው በድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ህልፈት የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ ለአገሪቱ ሕዝብ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ከዚህ ቀደም ሰኔ 16/2010 እንዲሁም ሰኔ 15/2011 ካጋጠሙት ክስተቶች ጋር በማዛመድ "በሦስቱ ሰኔዎች ጉዟችንን የማደናቀፍና ደም የማፍሰስ ሙከራዎች ተደርገዋል" ብለዋል።

በመቀጠልም በዚህኛው ሰኔ ከሁለቱ ሰኔዎች በተለየ መንገድ በቀጥታ ጉዳዩ የማይመለከተው ሰው እንዲገደል ተደርጎ ከፍተኛ ድንጋጤ፣ ከፍተኛ ጥርጣሬ እና የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር ሙከራ ተደርጓል ሲሉ ገልፀዋል።

"መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲገነዘብ የሚያስፈልገው ሃጫሉ የእኛ መታወቂያ ባይኖረውም ዩኒፎርም ባይለብስም ታጋይ ነው" ካሉ በኋላ "ታጋይ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይገነዘባል" ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም በሃጫሉ መስዋዕትነት የኢትዮጵያ አንድነት፣ የኢትዮጵያ ሰላም፣ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ጉዞ በአንጸባራቂ መንገድ ዳግም የሚመዘገብ እንጂ የሚቆም አይደለም በማለት፤ "የጠላቶቻችን መሻትና ፍላጎት እንዳይሳካ ሕዝቡ የዚህን እኩይ ተግባር አላማ በመረዳት ግብ እንዳይመታ" ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።

የሃጫሉ ሁንዴሳ ገዳዮች ጉዳይ በፍጥነት ተጣርቶ ፍትህ እንዲገኝ፣ የሕግ የበላይነት በአገር ደረጃ እንዲረጋገጥ እንዲሁም ሠላም የማስከበር ሂደቱ እንዳይደናቀፍ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም መንግሥት የዚህችን አገር ሉአላዊነት፣ ሠላም፣ ዘላቂ ፍላጎቷን ለማሳካት በእጅጉ እንደሚጥር አመልክተዋል።

ሰኞ ዕለት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በአትዮጵያና በጎረቤቶቿ ጉዳይ ላይ እየመከረ ባለበት ሰዓት መንግሥትን ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን አድርጎ የከፋ ውሳኔ እንዳይወሰን በሚጥርበት ሰዓት ሃጫሉ ሁንዴሳ በጥይት መገደሉን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሃጫሉን ". . .በቅርብ ለረዥም ዓመታት የማውቀው ወዳጄ . . ." በማለት ሃዘናቸው ጥልቅ መሆኑን ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ "ጠላቶቻችን" ያሏቸውን አካላት ሲገልፁ "የጠላቶቻችን ፍላጎት የጀመርነው እንዳይሳካ። የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ብሔሮች ጋር በዚሁ ምክንያት ደም እንዲቃባ" እንደሚፈልጉ በመግለጽ ይህንንም ለማሳካት በተደጋጋሚ ሙከራ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አክለውም "በሰኔ ወር አዲስ አበባ ላይ ጀምረን አዲስ አበባ ጦርነቱን እንጨርሰዋለን፤ የሚያሰጋን የአሮሚያ ጉዳይ ነው" በማለት ሲቀሰቀስ እንደነበር በማስታወስ፣ ከዚያም "ገዳይ ቡድኖችን እያደራጁ ሲያሰማሩ እንደነበር መንግሥትም ሲያከሽፍ መቆየቱን" ገልፀዋል።

የእነዚህ ቡድኖች ፍላጎት ሃጫሉን ብቻ መግደል ሳይሆን ሌሎች የኦሮሞ ታዋቂ ሰዎችን ጭምሮ በመግደል "በብሔሮች መካከል ቁርሾንና ግድያን ለመፍጠር፣ አንድነታችን እንዲናጋ፣ ሠላማችን እንዲደፈርስ፣ ያሰብናቸው ጉዳዮች እንዳይሳኩ የውስጥና የውጪ ጠላት በመቀናጀት ይህንን እኩይ ተግባር ፈጽመዋል" ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም የሃጫሉ አስከሬን ወደ ትውልድ ቀዬው አምቦ ሲሄድም እነዚሁ አካላት እንዲስተጓጎል በማድረግ በርከት ያሉ ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በህልፈተ ህይወታቸውም የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልፀዋል።