የሃጫሉ ግድያን ተከትሎ በአዳማ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ አምስት ሰዎች ሞቱ

የአዳማ ከተማ
የምስሉ መግለጫ, የአዳማ ከተማ

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በአዳማ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ አምስት ሰዎች በጥይት ተመትተው መሞታቸውን የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር መኮንን ፈይሳ ለቢቢሲ አረጋገጡ።

ሜዲካል ዳይሬክተሩ ግለሰቦቹ ሆስፒታል ከመድረሳቸው በፊት መሞታቸውን ተናግረዋል።

ዶ/ር መኮንን አክለውም 75 ሰዎች ቆስለው በሆስፒታሉ እንደሚገኙ የገለፁ ሲሆን ከአርሲ ዴራ ደግሞ 19 ሰዎች ተጎድተው ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውንና የተወሰኑት በእሳት ቃጠሎ መጎዳታቸውን አስረድተዋል።

በአዳማ በነበረ ተቃውሞ የመንግሥት ህንጻዎች መቃጠላውን የቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና በጭሮ በነበረ ተቃውሞ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን የከተማዋ ሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በአዳማ ከተማ ከምሳ ሰዓት በፊት የነበረው አለመረጋጋት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ወዲህ ጋብ ማለቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢበሲ ገልፀዋል።

የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደልን ተከትሎ ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ በኦሮሚያ አንዳንድ ከተሞች ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን በዚህም የተነሳ የተለያዩ ጉዳቶች በሰውና በንብረት ላይ መድረሱ እየተሰማ ነው።