ኢትዮጵያ፡ አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, ullstein bild
በኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች አረጋገጡ።
ዛሬ ማክሰኞ ከረፋድ ጀምሮ የቢቢሲ የኢንተርኔት እንቅስቃሴ መረጃ እንደሚያመለክተው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የተጠቃሚዎች ቁጥር አሽቆልቁሏል።
ይህንንም ተከትሎ በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር፣ በመቀሌና ነቀምቴ የሚገኙ ነዋሪዎችን በማናገር በተደረገው ማጣራት የኢንትርኔት አገልግሎት መቋረጡን ቢቢሲ ለመረዳት ችሏል።
የኔት ብሎክስ ኤክስኪውቲቭ ዳይሬክተር አልፕ ቶከር ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት በመላው ኢትዮጵያ "ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስችል መልኩ" ኢንተርኔት መቋረጡን አጋግጠዋል።
እርምጃው ሆን ተብሎ የተደረገ እና ቀጣይ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በአካባቢው የቴክኒክ ችግር አለመኖሩን ገልፀዋል።
ኃላፊው የኢንተርኔት መቋረጡን አስመልክቶ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ተጽዕኖም ሰያስረዱ ከባለፈው አመት የአማራ ክልል ባለስልጣናት እና የከፍተኛ ወታደራዊ ሹማምንቶች ግድያ ወዲህ የታየ ከፍተኛ አገር አቀፍ ተጽእኖ ያለው ነው ብለዋል።
ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ውስጥ በጥይት የተገደለውን ታዋቂው የኦሮምኛ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዛቸውን ከነዋሪዎች ቢቢሲ ተረድቷል።
የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ሐዘናቸውን ለመግለጽ እንዲሁም አስከሬኑን ወደ ትውልድ ከተማው አምቦ ለመሸኘት የተሰባሰቡ በርካታ የድምጻዊው አድናቂዎች በአንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች ላይ በከፍተኛ ቁጥር መታየታቸውን የቢቢሲ ሪፖርተሮች ገልጸዋል።
የኢንተርኔት መቋረጥ ከድምጻዊው ግድያ በተያያዘ ካለው እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ የታወቀ ነገር ባይኖርም፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት መንግሥት አለመረጋጋትና የጸጥታ ስጋቶች የሚላቸው ክስተቶች ሲያጋጥሙ በኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ አጋጥሟል።
















