የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የ78 ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ተገለጸ

ሃጫሉ ሁንዴሳ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የታዋቂው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተከሰተ አለመረጋጋት የ78 ሰዎች ህይወት ማለፉን ክልሉ አስታውቋል።

ከነዚህም መካከል ሶስቱ የመንግሥት የፀጥታ አስከባሪ ኃይል አባላት መሆናቸውንም የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ቢቢሲ ለየኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ጥዋት በደወለበት ወቅት ከሃጫሉ ሞት ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ተቀስቅሶ በነበረው ተቃውሞ ቢያንስ 67 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች መቁሰላቸውን አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በበኩላቸው ትናንት ማታ በሰጡት መግለጫ በዜጎች ላይ ደረሰ ባሉት ጉዳት "ትናንት እና ዛሬ 8 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል" ያሉ ሲሆን ፣ ነዋሪዎች ህይወታቸው ያለፈው "በቦምብ፣ ጥይት፣ በድንጋይ እና በመሳሰሉት ነው" ብለዋል።

አክለውም የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖሊስ አባላት ላይ ከቀላል እስከ ሞት ድረስ ጉዳት ደርሶባቸዋል ያሉት ኮሚሽነሩ "ዛሬ [ረቡዕ] እና ትናንት [ማክሰኞ] 57 የሚሆኑ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት ደርሷል" በማለት ሁለት አባላት ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

በሺህዎች የሚቆጠሩ አድናቂዎቹ የድምጻዊውን አስከሬን ለመሸኘትና ዛሬ በሚፈጸመው በቀብሩ ላይ ለመገኘት አምቦ ከተማ ውስጥ መሰብሰባቸው ተገልጿል።

ማክሰኞ ዕለት የፌደራል ፖሊስ ፖለቲከኛውን ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 35 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገለጸ ሲሆን ትናንት ደግሞ የባልደራስ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆነውን እስክንድር ነጋን ይዞ ማሰሩን አሳውቋል።

ፖሊስ ከግድያው ጋር ተያያዘ ሁለት ተጠርጣሪዎችን መያዙን ቢገልጽም እስካሁን ሃጫሉ በማንና ለምን እንደተገደለ የተገለጸ ነገር የለም።

"የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላትን ጨምሮ አስከ ትናንት ማክሰኞ ቢያንስ 67 ሰዎች ተገድለዋል" ሲሉ የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በርካታ ሰዎች በከባድ ሁኔታ መቁሰላቸውና በንብረትም ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አቶ ጌታቸው ባልቻ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ማክሰኞ ረፋድ ላይ አለመረጋጋቱ እየተባባሰ ወደ ሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች ሲዛመት መንግሥት የኢንተርኔት አገልግሎትን እንዲቋረጥ አድርጓል።

ትናንት ረቡዕም የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የትውልድ ከተማ በሆነችው አምቦ ውስጥ በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ አምስት ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናትና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ዱላና ብረት የያዙ በቡድን የተሰባሰቡ ሰዎች በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ጥቃትና ዘረፋ የመፈጸም አዝማሚያ በመታየቱ መንግሥት የጦር ሠራዊቱን በመዲናዋ እንዳሰማራ ሮይተርስ ዘግቧል።