ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ማን ነው?

ሃጫሉ ሁንዴሳ

የፎቶው ባለመብት, MARSAALEE HAWAASAA

ሃጫሉ ሁንዴሳ ተወልዶ ያደገው ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አንድ መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምተገኘው አምቦ ከተማ ውስጥ ነው።

እናቱ ወይዘሮ ጉደቱ ሆራ፣ ሃጫሉ ከልጅነቱ ታሪክን መስማትና የመንገርና ዝንባሌውንና ችሎታውን ጠንቅቀው ተረድተውት ስለነበር ከመጀመሪያው አንስቶ ያበረታቱት እንደነበር በተደጋጋሚ ሃጫሉ ያስታውሳል።

አባቱ አቶ ሁንዴሳ ቦንሳ ደግሞ ልጃቸው ሃጫሉ በትምህርቱ ዓለም ገፍቶ ዶክተር ወይም የዩኒቨርሲቲተ መምህር እንዲሆንላቸው ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው።

ሃጫሉ ግን ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በፍቅሯ ለወደቀላት ሙዚቃ ነበር መላው ትኩረቱ። በአስራዎቹ እድሜው ላይ እያለ እንኳን የበርካቶችን ስሜት የሚኮረኩሩ ሙዚቃዎችን ይጫወት ነበር።

ሃጫሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ በ1995 ዓ.ም የ17 ዓመት ታዳጊ እንዳለ ታስሮ ለአምስት ዓመታት አምቦ በሚገኘው እስር ቤት አሳልፏል።

ፖለቲካዊ መልዕክት ያላቸውና ተወዳጅ የኦሮሞ የትግል ሙዚቃዎችን ማቀንቀኑን እንዲያቆም ለማድረግ መታሰሩን ሃጫሉ ይናገራል።

ነገር ግን መታሰሩ እንደውም ይበልጥ በሥራው እንዲገፋበትና በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ግፍ እና ጭቆና የበለጠ እንዲገባው ማድረጉን በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር።

በእስር ላይ ሳለም ነበር የሙዚቃ ግጥሞችን ዜማዎችን መጻፍ የጀመረው። ከአምስት ዓመታት በኋላ ሲለቀቅ የደረሰበትን በደል ለመቃወምና ለሚሊየኖች ድምጽ ለመሆን ወስኖ እንደወጣ ይናገራል ሃጫሉ።

በአጭር ጊዜም በኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በመላዋ አገሪቱ ተወዳጅ የሆነለትን 'ሳኚ ሞቲ' የተሰኘውን አልበሙ አቀረበ። የዚህ የሙዚቃ ስብስብ አብዛኛዎቹ ግጥሞችና ዜማዎች ሃጫሉ በእስር ላይ እያለ የሰራቸው እንደነበሩ ይነገራል።

በወቅቱ በሃያዎቹ መጀመሪያ የእድሜ ክልል ውስጥ የነበረው ሃጫሉም በዚህ አልበሙ በተለይ ደግሞ የአልበሙ መጠሪያ በነበረው ሙዚቃው ቋንቋውን በማይችሉ ሰዎች ዘንድም ታዋቂነትን ለማትረፍ ችሎ ነበር።

ከጥቂት ዓመት በኋላም ወደ አሜሪካ የሙዚቃ ሥራዎቹን ለማቅረብ በሄደበት ጊዜ ሁለተኛውንና "ዋኤ ኬኛ" አልያም "የእኛ ነገር" የሚል ትርጉም ያለውን አልበሙን ለቀቀ።

በወቅቱ አልበሙ አማዞን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ በመሸጥ ከፍተኛ ትኩረትን አግኝቶ የነበረ ሲሆን፤ የሃጫሉ ተወዳጅነትም የበለጠ እየተጠናከረ መጣ።

ሃጫሉ እንደሚለው "ሙዚቃ ለእኔ ህይወቴ ነው። ውስጤ ነው ያለው። የሕዝቤን የአኗኗር ዘዬ የማሳውቅበት፣ የሆዴን የምገልጽበት ነው። ሙዚቃ ሁሉ ነገሬ ነው፤ ዘመድም ጠላትም ያፈራሁበት።"

ሃጫሉ ተወዳጅ የሆኑ የኦሮሞ የሙዚቃ ስልቶችን ከዘመናዊው ሙዚቃ ጋር በማጣመር በሚያቀርባቸው ሥራዎቹ ብዙዎችን ጆሮና ቀልብ ለመማረክ አስችሎታል። በአገሪቱ የሚገኙ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ሙዚቃዎቹን በተደጋጋሚ በማጫወታቸው በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ዘንድ አድናቆትን ማግኘት ችሏል።

ከሦስት ዓመት በፊት በአገሪቱ ተቀስቅሶ ከነበረው ጸረ መንግሥት ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ በነበረው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ወቅት የሃጫሉ ያወጣው 'ማላን ጂራ' የተሰኘው ነጠላ ሙዚቃው ከፍተኛ ተወዳጅነትን ከማትረፍ አልፎ የእንቅስቃሴው መነቃቂያ ሆኖ ነበር።

ሃጫሉ የመንግሥት ባለስልጣናት በሚገኙባቸውና በቀጥታ በቴሌቪዥን በሚቀርቡ በትልልቅ የሙዚቃ መድረኮች ላይ በመገኘት ሙዚቃዎቹን በሚያቀርብበት ጊዜ ያለፍርሃት የሚሰማውን ፖለቲካዊ ጉዳዮችንም በማቅረብ በድፍረቱ ይታወቃል።

ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት የነበረው የ36 ዓመቱ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሰኞ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ በተፈጸመበት ጥቃት ህይወቱ አልፏል።