"13 ሰው የገደልኩት 'ጄሪ' የሚባል መንፈስ ግደል ብሎኝ ነው"

ጆሴፍ ጄምስ ዲአንጄሎ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የእኚህ አዛውንት ሙሉ ስም ጆሴፍ ጄምስ ዲአንጄሎ ይባላል። የአሜሪካ ሚዲያ የሚያውቃቸው ግን 'ወርቃማው ነፍሰ ገዳይ' በሚለው ቅጽል ስማቸው ነው።

አሁን 74 ዓመት አልፏቸዋል። እጃቸው በደም ተጨማልቋል። ብዙዎቹን ወንጀሎች የፈጸሙት በፈረንጆቹ በ1970ዎቹና 80ዎቹ አካባቢ ነው። በዚያ ዘመን ዘርፈዋል፣ ደፍረዋል፣ ገድለዋል። የፈጸሙትን ወንጀል ብዛት እርሳቸውም ዘንግተውታል። ፖሊስም ታክቶት ነበር። የሟች ቤተሰብ ብቻ ነው ያልዘነጋው።

ዲ አንጄሎ የሚሉት 'ጄሪ' የሚባል ስም ያለው አንዳች ውስጤ የተቀመጠ መንፈስ ነው ሰዎችን አሰቃይቼ እንድገድላቸው የሚያዘኝ ይላሉ።

በካሊፎርኒያ ከዓመታት በፊት ማን እንደሚፈጽማቸው የማይታወቁ ግድያዎች እዚያም እዚህም ይታዩ ነበር።

ፖሊስ ወንጀለኛውን ሊደርስበት ሳይችል ቆይቷል። ሰው ይገደላል፣ ሴቶች ይደፈራሉ፣ ገንዘብ ይዘረፋል፤ ወንጀለኛው ግን አንዳች ዱካ ሳይተው ይሰወራል። ይህ በመሆኑ ነው 'ወርቃማው ነፍሰ ገዳይ' በሚል ቅጽል ብቻ ማንነቱ ያልታወቀ ወንጀለኛ ሲፈለግ እንዲኖር ያደረገው።

በመጨረሻ ያን ሁሉ ወንጀል የፈጸሙት ሰው ጆሴፍ ጄምስ ዲ አንጄሎ መሆናቸው ተደረሰበት።

ዴአንጄሎ ሕግ አስከባሪ ፖሊስ ነበሩ። በጎልማሳነት ዘመናቸው። በወጣትንት ዘመናቸው ቬትናምም ዘምተዋል።

ከቬትናም መልስ ነው ፖሊስ የሆኑት። ካሊፎርኒያን እንደርሳቸው ያሸበረ የለም ነው የሚባለው። ይዘርፋሉ፣ ይደፍራሉ፣ ይገድላሉ። የገደሏቸው ሰዎች ብዛት ደርዘን ያልፋል። ይህን ሁሉ አድርገው ታዲያ ለዚህ ሁሉ ዓመታት አልተደረሰባቸው ነበር።

ዲ አንጄሎ ታዲያ ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ ፍርድ ቤት ቀርበው 'አዎ እኔ ነበርኩ ስገድል የኖርኩት፣ ጥፋተኛ ነኝ' ሲሉ አምነዋል።

ጆሴፍ ጄምስ ዲ አንጄሎ በቁጥጥር ስር የዋሉት በ2018 ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቃል ተናግረው አያውቁም ነበር። ዝም ጭጭ እንዳሉ ቆዩ።

ከዚያ በኋላ የሆነ ሰዓት ላይ፣ 'ጥፋተኛ ነኝ፣ ድርጊቱን ፈጽሚያለሁ' የሚሉ ቃላትን ብቻ ደጋግመው ያለማቋረጥ መናገር ጀመሩ።

ፍርድ ቤት ቀርበውም ይህንኑ ነው ያሉት። ድርጊቱን ስለመፈጸማቸው ማመናቸው የሞት ፍርድን ያስቀርላቸዋል። ሆኖም ዕድሜ ልክ እስር ፍርድ ተሰጥቶባቸዋል። ምህረትም አመክሮም የሌለው እስር።

ዲ አንጄሎ በ1980ዎቹ አጋማሽ ስለፈጸሟቸው ወንጀሎች እንደተናዘዙት ከሆነ ድፈር፣ ዝረፍ ግደል ሚለኝ 'ጄሪ' የሚባል ውስጤ የተቀመጠ መንፈስ ነው ብለዋል።

"ውጣልኝ ለማለት አቅሙ አልነበረኝም። አብሮኝ ነበር የሚኖረው፣ አብሮኝ ነው የሚሄደው፣ የሚበላው የሚጠጣው፣ ጭንቅላቴ እርሱ ነበር፣ ጄሪ አድርግ ካለኝ ውጪ ማድረግ አልችልም ነበር፤ እሱ ነው ግደል እያለ ሰዎቹን ያስፈጀኝ። አሁን እሱ ወጥቶልኛል፣ ለጥፋቴ ዋጋ መክፈል ጀምሪያለሁ፣ ደስተኛ ነኝ" ብለዋል ሰውየው።

የዲ አንጄሎ ፍርድ የታየው በአንድ ዩኒቨርስቲ ትልቅ አዳራሽ ነው። በርካታ ሰው በመገኘቱና መራራቅ ግድ ስለሚል ነበር ይህ አዳራሽ ፍርድ ለማስቻል የተመረጠው።

ሰውየው ዊለቸየር እየተገፉ ነበር ፍርድ ቤት የመጡት። በ13 ሰዎች ግድያና ሌሎች በርካታ የመድፈር ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለዋል፣ እርሳቸውም 'አዎ ነኝ' ብለዋል።

የሟች ቤተሰቦች በአዳራሹ የተገኙ ሲሆን ለቅሷቸው ችሎቱን ሲረብሽ ነበር።

ለምሳሌ በአዳራሹ ከተገኙት ውስጥ ጄኒፈር ካሮል አንዷ ነበረች።

የሕግ ሰው የነበረው አባቷ ላይማን ስሚዝ በ1980ዎቹ በእኚህ ሰውዬ ተገድለውባታል። እናቷም የተገደሉት በሰውዬው ከተደፈሩ በኋላ ነበር። ጄኔፈር እንባዋን መቆጣጠር አልቻለችም።

ሞገደኛው ሽማግሌ ወንጀለኛ ዲ አንጄሎ ከዚህ ሁሉ ግፍና ግድያ በኋላ በሰላምና በጤና ሲኖሩ ነበር። ፖሊስ ለዚህ ሁሉ ወንጀል ተጠያቂ በጭራሽ እርሳቸው ይሆናሉ ብሎ አስቦ አያውቅም ነበር።

ፖሊስ እንዴት ደረሰባቸው?

ፖሊስ ሰውየውን ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ ሊደርስባቸው የቻለው በዲኤንኤ (የዘረመል ዱካ) አማካኝነት ነው።

ያኔ ድሮ ወንጀሎ ከተፈጸመባቸው ስፍራዎች የተገኘው የዘረመል ቅንጣት ጋር የሚመሳሰል የሩቅ ዘመድ እንኳ ቢኖር በሚል ፖሊስ በበይነ መረብ የፍለጋ ሙከራ ጀመረ።

አንድ የዘረመል ሰንሰለትን የሚያጠራቅም ዝነኛ ድረ ገጽ አለ። ይህ ቋት የዘረመል ቅንጣት ሰንሰለትንና የሰዎችን ዘርማንዘር በመዘርዘር ይታወቃል። ይህን ድረ ገጽ ፖሊስ እንደ ድንገት ሲፈትሽ የሰውየውን የዘመድ አዝማዶች ሰንሰለት ያገኛል። ሰንሰለቱን ተከትሎ ሲሄድ እኚህ ሰው ጋር ያደርሰዋል።

ከዚያ በኋላ ፖሊስ በድብቅ ወደ ዲ አንጀሎ ቤት ይሄድና የእርሳቸው መኪና ጋር ሲደርስ ይቆማል። ከመኪናቸው በር ላይ የዘረመል ቅንጣት ይወስድና ድሮ ወንጀሎቹ ከተፈጸመባቸው ስፍራዎች ከተገኘው ቅንጣት ጋር ሲያመሳስለው አንድ ሆኖ ይገኛል።

እርግጠኛ ለመሆን ዲ አንጀሎ አፉን የጠረገበት ሶፍት መኪና አጠገብ ወድቆ ስለነበር ይህንን አግኝቶ ከወርቃማው ወንጀለኛ ጋር ሲያመሳስለው አንድ ይሆናል። በዚህን ጊዜ ነበር ዲ አንጄሎ መጎደኛው ወንጀለኛ ስለመሆናቸው መቶ በመቶ የተረጋገጠው።

ሽማግሌው ዴ አንጄሎ በነሐሴ ወር መጨረሻ ፍርድ ቤት በይፋ ዕድሜ ልክ ይፈርድባቸዋል። ዓለምን ለ45 ዓመታት ሲያነጋግር የኖረው ምስጢርም ፍጻሜውን ያገኛል።