ሕንድ አዲስ የኮሮና ክትባትን በሰው ላይ ልትሞክር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአገራቸው በምርምር ላይ የቆየውን የመጀመሪያው ክትባት ፍቃደኛ በሆኑ ሕንዳዊያን ላይ ከቀናት በኋላ ሙከራ ማድረግ እንደሚጀመር ተገለጸ።
ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆኑ ያልተገለጹት እኒህ ሕንዳዊያን ክትባቱ የሚሰጣቸው በሐይድራባድ በሚገኝ ባራት ባዮቴክ በተሰኘ የጥናት ድርጅት ነው።
ክትባቱ በእንሰሳት ላይ በተደረገ ሙከራ ምንም የጎንዮሽ ጉዳት ያላስከተሉ ከመሆኑ በላይ የተፈጥሮ በሽታን የመከላከያ ኃይል ቫይረሱን የሚከላከሉ ህዋሶችን እንዲያመርት አስችሎታል።
በመላው ዓለም በቤተ ሙከራ ደረጃ ያሉ 120 የክትባት ምርምሮች ሲኖሩ ከነዚህ ውስጥ ስድስቱ በሕንድ ነው እየተካሄዱ የሚገኙት።
ይህ ክትባት የሚመረተው ከራሱ ከኮቪድ-19 ሲሆን ቫይረሱ በቤተ ሙከራ ውስጥ ተዳክሞና መጠኑ ቀንሶ ነው ወደ ክትባትነት የሚለወጠው።
የሕንድ የመድኃኒት ቁጥጥር አስተዳደር ለባራት ባዮቴክ ምርምር ተቋም የምዕራፍ አንድና ምዕራፍ ሁለት ሙከራዎችን በሰው ላይ እንዲያደርግ የፈቀደው በእንሰሳት ላይ የተደረገው ሙከራ አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን ከመረመረ በኋላ ነው።
እነዚህ ሁለት ምዕራፎች የተከፈሉ ሙከራዎች ትኩረት የሚያደርጉት የክትባቱ ፈዋሽነት ላይ ሳይሆን ክትባቱ በሰው ልጅ ላይ ጉዳት ያስከትላል ወይስ አያስከትልም በሚለው ላይ ነው።
አዲሱ ሕንድ የሰራችው ክትባት ኮቫክሲን የሚል ስም የተሰጠው ሲሆን በቤተ ሙከራ የተዘጋጀው ደግ ከብሔራዊ የሕንድ ቫይሮሎጂ ኢንስቲትዩትና ከካውንስል ኦፍ ሜዲካል ሪሰርች ጋር በመተባበር ነው።
ይህ ተቋም ከዚህ ቀደም ኤችዋን ኤንዋን ለተሰኘ ቫይረስ 4 ቢሊዮን ጠብታ ክትባት በመላው ዓለም አምርቶ ያሰራጨ ነው።
ሕንድ የዓለም ትልቋ የመድኃኒት አምራች አገር ናት።

















