'ጀግናዬ" የሚለውን የወዳጁን ቀብር በቴሌቪዥን የተከታተለው የሃጫሉ ሁንዴሳ ጓደኛ

ታዋቂው ሙዚቀኛ ሃጫሉ ሁንዴሳ በጥይት ተመትቶ ከተገደለ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ለቀናት የቆየ አለመረጋጋት ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን በወቅቱ በነበሩ ግጭቶችም ቢያንስ 80 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የሃጫሉ ሙዚቃዎች ብዙ ጊዜ ፍቅርና አንድነትን የሚሰብኩ የነበሩ ሲሆን በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የነበሩ ብሶቶችንም በማቀንቀን ይታወቃል።
የቢቢሲው የካሜራ ባለሙያ አመንሲሳ ኢፋ ከሃጫሉ ጋር የቅርብ ወዳጅ የነበረ ሲሆን ከዓመታት በፊት ሽልማቶችን ማሸነፍ የቻለ ሙዚቃው ላይ የቀረጻውን ሥራውን አብሮ አከናውኗል።
ስለሞቱ እንዴት እንደሰማና ስለነበረው ሁኔታ ሲያስታውስ "አንዳንዴ ስለ ሃጫሉ ሞት ሳስብ ምናለ እሱ በሕይወት ተርፎ እኔ በሞትኩኝ እላለሁ። ለበርካቶች እሱ ጀግና ነበር፤ ገና ብዙ ከእሱ እጠብቅ ነበር" ይላል።
ለሕዝቡ ተዋግቷል፤ በርካታ ሙዚቀኞች፣ አርቲስቶች፣ ተሟጋቾችና ፖለቲከኞች የነበረውን ሁኔታ ሸሽተው ከአገር ሲወጡ፣ ሃጫሉ ማንም የማያነሳቸውን ሀሳቦች እያነሳ አገር ውስጥ ነበር የቆየው።
‘ሃጫሉ ሆስፒታል ገብቷል’
ሰኞ ምሽት ላይ ሃጫሉ ምን ሆነ የሚሉ ጥያቄዎች በአጭር የጽሑፍ መልዕክቶች ለአመንሲሳ መድረስ ጀመሩ። በሰዓቱ ማንም ሕይወቱ አልፋለች የሚል አልነበረም፤ ነገር ግን የሆነ ነገር እንደተከሰተ ግልጽ ነበር።
አንዳንድ ጓደኞቼን በስልክ ለማግኘት ሞከርኩኝ ነገር ግን አልተሳካልኝም። ከዚያም አንድ ሰው ሃጫሉ ሆስፒታል እንደሚገኝ መልዕክት ላከልኝ።
ወዲያው ወደሚገኝበት ሆስፒታል እየሄድኩ ሳለ አንዱን ጓደኛዬን በስልክ ማግኘት ቻልኩ፤ እሱም በስልክ እንባ እየተናነቀው ከሃጫሉ አስከሬን አጠገብ እንደሚገኝ ነገረኝ።
ልክ ሆስፒታል ስደርስ አስክሬኑ የሚገኝበት አካባቢ ብዙ ሰዎች ተሰብስበዋል፤ ከባድ የለቅሶ ድምጽም ይሰማ ነበር። የሆነ ሰው የተሸፈነበትን ጨርቅ ሲገልጥ ደረቱ ላይ በጥይት የተመታውን ተመለከትኩ።
በቦታው ፖሊስም በርካታ ወዳጆችም ነበሩ። ስሙን እየጠራሁ አለቀስኩ። ሁሉም ሰው ይጮሀል፤ ሁሉም ሰው ያለቅሳል።
የሃጫሉ አስከሬን ለተጨማሪ ምርምራ ወደ ሌላ ሆስፒታል ሲወሰድ አምቡላንሱን ተከተልነው። እስከ ሌሊቱ አስር ሰዓት ድረስ እየጠበቅን ነበር።
ዜናውን የሰሙ በርካቶችም በሆስፒታሉ አቅራቢያ መሰባሰብ ጀምሩ። ሁሉም ስሙን እየጣራ እንባውን ያፈስ ነበር።
የጠዋት ፀሐይ ከወጣች በኋላ ደግሞ አስክሬኑን ከአዲስ አበባ አስወጥተን 100 ኪሎሜትር በምትርቀውና ወደ ትውልድ ከተማው አምቦ ለመውሰድ ጥረት አደረግን።
ከአዲስ አበባ ስንወጣ ነገሮች ተቀያይረው ነበር። እዚህም እዚያም ችግር ተፈጥሮ ነበር። በየመንገዱ ተቃውሞዎች የነበሩ ሲሆን ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ሲተኩስ የተኩስ ድምጽም እሰማ ነበር።
ልክ ቡራዩ ስንደርስ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሕዝብ ማመላሻዎችና በእግራቸው ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ አገኘናቸው። ሀዘናቸውን ለመግለጽና ያላቸውን ክብር ለማሳየት ነበር ያን ሁሉ መንገድ ተጉዘው የመጡት።
ሁሉም ከተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች የመጡ ሲሆን፤ የሃጫሉን ሞት ከሰሙ በኋላ ሌሊቱን በሙሉ በእግራቸው ሲጓዙ የነበሩ በርካቶችም ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቀብር ሥነ ሥርዓቱ አዲስ አበባ መሆነ አለበት የሚሉም ነበሩ።
መኪናዬ ውስጥ ሆኜ ሰዎች "ሃጫሉ የአገራችን ጀግና ነው’’ ሲሉ አሰማለሁ። "በአዲስ አበባ የጀግና አቀባበር ሊደርገግለት ይገባል" የሚሉም ነበሩ።
ለጥቂት ጊዜ ከቆምን በኋላ አስክሬኑን ይዘን ወደ አዲስ አበባ መመለስ ጀመርን።
በኋላ ላይ መንግሥት ሃጫሉ አምቦ ነው መቀበር ያለበት ማለቱንና ቤተሰቡም የቀብር ሥነ ሥርዓቱ አምቦ ውስጥ እንዲሆን ፍላጎት አላቸው መባሉን ሰማን።
ከዚያም አስክሬኑ በሄሊኮፕተር ወደ አምቦ ከተማ ተወሰደ።
ነገር ግን ሐሙስ ዕለት ወደ አምቦ የሚወስደው መንገድ በመዘጋቱ የሃጫሉ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት ሳልችል ቀረሁ። በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ በርካታ ሰዎች የተገኙ ሲሆን በቀጥታ ስርጭትም ይተላለፍ ነበር።
እኔም ቀብሩን በቴሌቪዥን ለመከታተል ተገደድኩ፤ ሁኔታው ለእኔ በጣም አስቸጋሪ ነበር።
በተገቢው መንገድ ለመሰናበት በቀብሩ ላይ መገኘት ነበረብኝ። ከቀጥታ ስርጭቱ እንደተመለከትኩ በቀብሩ ላይ እምብዛም በርካታ ሰዎች አልነበሩም። በእኛ ባህል አይደለም እንደዚህ አይነት የአገር ጀግና ይቅርና አንድ ተራ ሰው እንኳን ሕዝብ ተሰብስቦ ነው የሚቀብረው።
ሁኔታውን በቴሌቪዥን እያየሁ አነባሁ።
ከዚያም ለእናቴ ደወልኩላት እና "ዛሬውኑ መሞት እፈልጋለሁ" አልኳት። እሷም በጣም እያለቀሰች ነበር። ከዚያች ቀን በኋላ ማንም ሰው "እንዴት ነህ?" እያለ ሲጠይቀኝ ማልቀስ ነው የሚቀናኝ።
ሌላው ቢቀር ሐሙስ ዕለት አንድ የሃጫሉ ጓደኛው የሆነ ነገር እንዳጋጠመው ስሰማ ለማጣራት ብዬ የደወልኩት ወደ ሃጫሉ ስልክ ላይ ነበር። ሁሉንም ነገር እስካሁን አልተቀበልኩትም።
ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘሁት ከህልፈቱ አንድ ሳምንት በፊት ነበር። ‘ኤሴ ጂርታ’ የሚል አዲስ ሙዚቃ እንዳዘጋጀና እንድሰማው እንደሚፈልግ ነግሮኝ ነበር።
የሃጫሉ ሥራዎች በፖለቲካ ብቻ የታጠሩ አልነበሩም፤ ስለ ባህል፣ ማንነት፣ አንድነት፣ ሰብአዊ መብትና ፍቅርን በተመለከተ በርካታ ሥራዎችን ለአድናቂዎቹ አበርክቷል።
ሃጫሉ ኩሩ የኦሮሞ ልጅ ነበር።
አንዳንድ ሰዎች ሃጫሉ ከአዲሱ አስተዳደር ወይንም ከብልጽግና ፓርቲ ገንዘብ ተቀብሏል በሚል ይወነጅሉት ነበር። እሱ ግን "ማንም እኔን አይገዛኝም" ይል ነበር።
ምንም እንኳን ከበርካታ ሰዎች ጋር አለመግባባት ውስጥ ቢገባም፤ እንዲሁም አዲስ አበባ ውስጥ ከሆኑ ሰዎች ጋር ጥሩ ያልሆነ ግንኙነት ቢኖረውም ለህይወቱ ፈርቶ አያውቅም። ሁሌም የሚለው አባባል ነበረው "ለሕዝብ ሲል የሚሞት ሰው ጀግና ነው" የሚል።
"እኔ ከማንም የተለየሁ አይደለሁም" ብሎኝ ነበር በአንድ ወቅት።

















