እስክንድር ነጋ 'ሁከትና ግጭት ለመቀስቀስ በመሞከር' ተጠርጥሮ መያዙ ተገለጸ

እስክንድር ነጋ

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚደንት እስክንድር ነጋ በአዲስ አበባ ውስጥ ሁከት ለመቀስቀስ በመሞከር ተጠርጥሮ እንደታሰረ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ምሽት ላይ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ጸጋ እንዳሉት በአዲስ አበባ ሁከትና ግጭት እንዲፈጠር በመቀስቀስ ተጠርጥሮ በሕግ ቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።

ኃላፊው እንዳሉት አቶ እስክንድር በአዲስ አበባ ውስጥ ቡድን በማደራጀት ወጣቶችን በተለያዩ ቦታዎች ላይ በመመደብ ሁከትን የሚያነሳሱ ቅስቀሳዎች ሲደረግ እንደነበር ጠቅሰዋል።

በዚህም በሕዝቡ መካከል ግጭትን ለመፍጠር በሚችሉ ድርጊቶች ተጠርጥሮ በሕግ ቁጥጥር ሰር መዋሉን አቶ ፈቃዱ ጸጋ ተናግረዋል።

የባልደራስ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ናትናኤል ያለምዘውድ ዛሬ [ረቡዕ] ከሰዓት በኋላ አቶ እስክንድር ነጋ በፖሊስ ተይዞ የተወሰደው ከቢሮው ነው ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አቶ እስክንድር አሁን የት እንዳለ እንደማያውቁ አቶ ናትናኤል ገልጸው፤ ምሽት ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባቀረበው ዜና ላይ ግን እስክንድር በቁጥጥር ስር የዋለው በአዲስ አበባ ውስጥ ሁከትና ግጭት ለመፍጠር በመሞከር ተጠርጥሮ እንደሆነ ተገልጿል።

ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ሰኞ ምሽት መገደሉ ከተሰማ በኋላ በተለያዩ ስፍራዎች አለመረጋጋት መከሰቱ ይታወቃል። ፡

ትናንት የድምጻዊውን አስክሬን ወደ ትውልድ ቦታው አምቦ ከተማ በማምራት ላይ እያለም የተፈጠረ ግርግርን ተከትሎ አቶ ጃዋር መሃመድን ጨምሮ 35 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሸን በጋራ በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡