በሰሞኑ የጸጥታ መደፍረስ ኦሮሚያና አዲስ አበባ የደረሱ ውድመቶች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የታዋቂው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተከሰተ አለመረጋጋት 80 ያህል ሰዎች ህይወት ማለፉን ክልሉ ለመገናኛ ብዙኀን በሰጠው መግለጫ ላይ አስታውቋል።
ከነዚህም መካከል ሶስቱ የመንግሥት የፀጥታ አስከባሪ ኃይል አባላት መሆናቸውንም በመግለጫው ወቅት ይፋ ተደርጓል።
የድምጻዊ ሃጫሉ የቀብር ስነስርዓትም ዛሬ በትውልድ ከተማው አምቦ ተፈጽሟል።
ነገር ግን ትናንትና በአምቦ የአርቲስት ሃጫሉ በአዲስ አበባ መሆን አለበት በሚል በተፈጠረው አለመግባባት ስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኦሮሚያ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ጅብሪል መሐመድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዛሬ የድምጻዊው የቀብር ስርዓት በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታ አካላት ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን የገለፁት በዚህም "ስኬታማ" እንደነበሩ ተናግረዋል።
የአርቲስት ሃጫሉ አስከሬን አሸኛኘት የተደረገለት በአምቦ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ሲሆን ይህም የሆነው ለቁጥጥር እንዲመች በሚል መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ጅብሪል አክለውም በሻሸመኔ፣ አዳባ፣ አዳማ እና ሌሎች ከተሞች ውስጥም በተፈጠረው ችግር የሰው ሕይወት ከመጥፋቱ ባሻገር ትልቅ የሚባሉ ንብረቶች መውደማቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የጠፋው ንብረት የግለሰቦችና የመንግሥት መሆኑን አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ሁከት በመፈጠሩ ሃብትና ንብረት መውደሙንና የተናገሩት አቶ ጅብሪል ከከተማ አስተዳደሩ ጋር አብረው እየሰሩ እንዳለም ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ኦሮሚያ ኮንዶሚኒየም በሚባል አካባቢ እና በሌሎች አካባቢዎች የተደራጁ ቡድኖች በግለሰቦችና ላይ ጉዳት የማድረስ ሙከራዎች እንደነበሩ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ትናንት ምሽት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን መግለጫ የሰጡት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች በነበረው አለመረጋጋትም "የግል እና የመንግሥት ተሽከርካሪዎችን መሰባበር እና ማቃጠል፣ የዜጎችን ያፈሩትን ሃብት እና ንብረት የመዝረፍ እንቅስቃሴ ነበር" ነበር ማለታቸው ይታወሳል።
ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው ላይ ንብረትነታቸው የግለሰብ እና የመንግሥት የሆኑ 250 ተሽከርካሪዎች ተሰባብረዋል፣ 20 ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል ሲሉም አክለዋል።
አቶ ጅብሪል በበኩላቸው ውድመቱ የተከሰተው በፅንፈኛ ብሔርተኞች ነው ሲሉ ይከስሳሉ።
"የወደመው ንብረት የአንድ ሕዝብ ብቻ አይደለም የተለያዩ ሕዝቦች ሐብት ነው" የሚሉት አቶ ጅብሪል፣ ውድመቱን ያደረሱ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ተናግረዋል።
ቡራዩ ከተማ ችግር ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ የነበረ ቡድን ሰውን ከመጉዳት አልፎ ከአምስት ፋብሪካዎች በላይ ለማቃጠል ሙከራ ሲያደርግ በፀጥታ ኃይል በቁጥጥር ስር ውለዋል ሲሉ ገልፀዋል።
በስተመጨረሻም ኃላፊው በኦሮሚያ ከሶስት መቶ በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች የተረጋጋ ሁኔታ መኖሩን ገልፀዋል።














