አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባ እንዲሁም በሃጫሉ ግድያ የተጠረጠሩ ሦስት ሰዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Family
በድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የተጠረጠሩ ሦስት ግለሰቦች እንዲሁም አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
በግድያው ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡት ሁለቱ ወንዶች አንዲት ሴት ሲሆኑ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸው ተገልጿል።
በተያያዘ ዜናም የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ባለፈው ማክሰኞ ከሰዓት በቁጥጥር ስር መዋላቸው የተገለጸው አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባ ዛሬ ጠዋት ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተነግሯል።
ከድምጻዊው የቀብር ሁኔታ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ ውዝግብን ተከትሎ በፖሊስ የተያዙት ሁለቱ ግለሰቦች ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ ቀጠሮ እንደተሰጠ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።
ሁለቱ ግለሰቦች ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት ለሰዎች ሞት ምክንያት የሆነን ሁከት በመቀስቀስና በሰው ሕይወት ማጥፋት ተጠርጥረው መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም መሰረት አቶ በቀለ ገርባ ለሐምሌ 6 ሲቀጠሩ አቶ ጃዋር መሐመድ ደግሞ ለሐምሌ 9 ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ወደ ማረፊያ ቤት መመለሳቸው ተነግሯል።
ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የአስከሬን ሽኝት መስተጓጎልና ከአንድ የፖሊስ አባል ግድያ ጋር በተያያዘ አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ ሌሎች 35 ሰዎች በቁጥጥር መዋላቸውን የፌደራልና እና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖች አስታወቀው ነበር።
ፖሊስ ጨምሮም ግለሰቦቹ በተያዙበት ጊዜ የጃዋር መሐመድ ጠባቂዎች ይዘውት የነበረው የጦር መሳሪያዎች እና መገናኛ ሬዲዮችንም መያዙንም ገልጿል።
አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባ የተቃዋሚው የኦሮሞ ፌደራሊስት ፓርቲ (ኦፌኮ) አባላት ሲሆኑ ፓርቲው የአባሎቹ መታሰር እንዳሳሰበው ትላንት ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።
የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በነበሩት ሁለት ቀናት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተከሰተ ግጭት ቢያንስ ከ70 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የክልሉ የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በዋና ከተማዋ አዲስ አበባም ሁለት የጸጥታ ኃይል አባላትን ጨምሮ የ10 ሰዎች ህይወት ማለፉን የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽን አሳውቋል።














