የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የቀብር ሥነ ሥርዓት አምቦ ውስጥ ተፈጸመ

ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ

የፎቶው ባለመብት, DAGI PICTURES

የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የቀብር ሥነ ሥርዓት በአምቦ ከተማ በሚገኘው የገዳመ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተፈጸመ።

ይሁን እንጂ አሁንም ድምጻዊው መቀበር ያለበት በአዲስ አበባ ነው በሚል ተቃውሟቸውን የሚያሰሙ በርካቶች ናቸው።

ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በመገኘት ሽኝት አድርገዋል።

በስታዲየሙ የተገኘው ሰው ቁጥር አነስተኛ እንዲሆን የተደረገው በደኅንነት ስጋት መሆኑ ተነግሯል።

ለቀብር ከአምቦ ዙሪያ የሚመጡ ሰዎች ወደ ከተማው እንዳይገቡም ተከልክለዋል። የመንግሥት የጸጥታ ኃይል መንገደኞች ወደ ከተማው እንዳይገቡ እና ወደ መጡበት እንዲመለሱ ለማድረግ አስለቃሽ ጭስ ሲተኩስ ነበር ተብሏል።

አንዳንድ ሰዎችም አስከሬኑ ወደሚቀበርበት ቦታ የሚወስዱ መንገዶችን የመዝጋት ሙከራዎች እንደነበሩና ቀብሩ ሊፈጸም የነበረበት ጉድጓድን መልሶ የመድፈን ሙከራዎችም መደረጋቸውንም የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትናንት በጥይት ተመትተው ህይወታቸው ያለፈው የሃጫሉ አጎት ቀብር በዛሬው ዕለት ቀደም ብሎ ተፈጽሟል።

ከአምቦ ከተማ ነዋሪዎች እንደሰማነው የክልሉ ፕሬዝድንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ይገኛሉ ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም መገኘት አለመቻላቸውን ተነግሯል።

ጸሎተ ፍትሐት

የፎቶው ባለመብት, ETV

ቀብር

የፎቶው ባለመብት, ETV