"ከዚህ በኋላ በየትኛውም ሚዲያ፤ . . . ሕዝብን ማዕከል ያደረገ የጥላቻ፤ የፕሮፖጋንዳ ሥራ አንታገስም" ታከለ ኡማ

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ሐሙስ ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ አዲስ አበባ ላይ እንዲደርስ ታስቦ የነበረው "እልቂት" ሙሉ በሙሉ መክሸፉን ተናገሩ።

አክለውም ከአርብ ጀምሮ ሁሉም የመንግሥትና መንግሥታዊ የሆኑ ድርጅት ሠራተኞች ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ አዝዘዋል።

"ከነገ [አርብ] ጀምሮ ሁሉም የመንግሥት ኃላፊዎች ሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ ሁሉም በከተማው ውስጥ የሚንቀሳቀስ የከተማው ነዋሪ መደበኛ ሥራውን እንዲጀምር አዛለሁ" ካሉ በኋላ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

በማሳሰቢያቸውም አገርም፣ ከተማም ትውልድም ሂደታቸውን ይቀጥላሉ ካሉ በኋላ "በዚህ ሂደቱ ላይ እንቅፋት እሆናለሁ፣ የጀመርኩትን ድራማ እቀጥላለሁ የሚልን በሕግም፣ በሥርዓትም፣ በሞራልም፣ በታሪክም እንፋረዳለን" ብለዋል።

አርቲስት ሃጫሉ "በተሰዋበት" ከተማ ላይ ከሥራ ባልደረቦቹና ከወንድሞቹ ጋር በመሆን መሃል ከተማ ላይ ለማስታወሻነት ሐውልት እንደሚቆም የተናገሩት ምክትል ከንቲባው፤የመታሰቢያ ሐውልቱም ድምጻዊውን የሚመጥን ብቻ ሳይሆን "ለዛሬው ትውልድ ስንቅና ቁጭት ሊፈጥር የሚችል ለሚቀጥለው ትውልድ ደግሞ ታሪክ" እንደሚሆን ተናግረዋል።

ምክትል ከንቲባው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ የከተማዋን ሰላምና ሥርዓት ማስከበር መጀመሩንም ተናግረዋል።

"ማናችንም ብንሆን ከአገር በታች ነን፣ ከሕግ በታች ነን" በማለት አገርንና ትውልድን ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ጠቅሰው፤ አገር የማስተዳደር ሂደትን ለማደናቀፍ የሚሞክር የትኛውም አካልን "ትዕግስት ልክ አለው" በማለት "ከዚህ በኋላ በየትኛውም ሚዲያ፤ በየትኛውም ጽሁፍ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ፤ ግለሰብን ማዕከል ያደረገ፤ ሕዝብን ማዕከል ያደረገ የጥላቻ፤ የፕሮፖጋንዳ ሥራ አንታገስም" ብለዋል።