የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ አስከሬን ከአዲስ አበባ ወደ ትውልድ ቦታው አምቦ ተመለሰ

በፖለቲካዊ ግጥሞቹ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ በትናንትናው ዕለት በጥይት ተመትቶ ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ ተቃውሞዎች ተከስተዋል።
የአርቲስቱ አስከሬን በበርካታ አድናቂዎቹ ታጅቦ ወደ አምቦ ሲያመራ የነበረ ቢሆንም በተገደለባት አዲስ አበባ አስከሬኑ ማረፍ አለበት የሚሉ ተቃውሞዎችም ነበሩ።
አስከሬኑ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ኦሮሞ ባህል ማዕከል መወሰዱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ሰዓት ወደ ትውልድ ቦታው አምቦ ተወስዶ ወላጆቹ ቤትም ይገኛል።
በተያያዘ ዜናም የፌዴራል ፖሊስ የ ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) አዲስ አበባ ስቱዲዮ "ጥሶ በመግባት ሠራተኞቹን እንዳሰረበት" የቴሌቪዥን ጣቢያው ይፋዊ በሆነው ፌስቡክ ገጹ ገልጿል።
ድምጻዊ ሃጫሉ በጥይት ተመትቶ መገደሉ ከተሰማ በኋላ በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን በመላው አገሪቱም የኢንተርኔት መቋረጥ ተከስቷል።
የተቃውሞ ሰልፍ ከተካሄደባው ከተሞች መካከል አዳማ አንዷ ስትሆን በከተማዋ አንዳንድ የመንግሥት ህንጻዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው የዓይን ምስክሮች ለቢቢሲ ሪፖርተሮች ገልጸዋል።
የአዳማ የሆስፒታል ምንጮች ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንዳረጋገጡት ወደ ሆስፒታል በጥይት ተመትተው የመጡ ሰዎች ሲኖሩ የሶስት ሰዎችም ህይወት አልፏል።
በተጨማሪም በአዳማ ከተማ ለተቃውሞ ወደ ኦቢኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲያመሩ የነበሩ ሰልፈኞች በጸጥታ ኃይሎች የተበተኑ ሲሆን፤ አንድ ሰው መቁሰሉን የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል።
ቢቢሲ ከጭሮ ማረጋገጥ እንደቻለው ሁለት ተቃዋሚ ሰልፈኞ በጥይት ተመትተው ሲሞቱ የመንግሥት ሕንጻዎችም ተቃጥለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የትውልድ አካባቢ በሆነው ጅማ ውስጥም ሰልፎች የተደረጉ መሆኑን ከቦታው ያናገርናቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል።












