በሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በቀጥታ ተሳትፈዋል የተባሉ ግለሰቦችና ቡድን በዐቃቤ ሕግ ይፋ ተደረጉ

ሃጫሉ

የፎቶው ባለመብት, Family

ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ውስጥ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ ሦስት ሰዎች መለያታቸውንና ሁለቱ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ይፋ አደረገ።

የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ዐቃቤ ሕግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ዛሬ አርብ በሰጡት መግለጫ ላይ ላይ እንዳስታወቁት በግድያው ውስጥ በቀጥታ እጃቸው አለበት ያሏቸውን የሦስት ሰዎች ማንነትና ከግድያ ጀርባ አለ የተባለውን ቡድንም ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት በድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ ናቸው ብለው በስም የጠቀሷቸው ሦስት ግለሰቦችን፤ ጥላሁን ያሚ፣ አብዲ አለማየሁና ከበደ ገመቹ የተባሉ ናቸው።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንዳሉት ሃጫሉ ሁንዴሳን በጥይት ተኩሶ የገደለው ጥላሁን ያሚ የተባለው ግለሰብ እንደሆነና ቀሪዎቹ ግለሰቦች አብዲ አለማየሁና ከበደ ገመቹ ደግሞ በግድያው ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ጨምረውም ሦስቱ ግለሰቦች የግድያውን ተልዕኮ ኦነግ-ሸኔ ከተባለው ቡድን ተቀብለው ማስፈጸማቸውን በመግለጽ፤ ቡድኑ ከግድያው ጀርባ እጁ እንዳለበት ዐቃቤ ሕጓ ተናግረዋል።

ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ተኩሶ የገደለው ጥላሁን ያሚ የተባለው ግለሰብ እንደሆነ ያመለከቱት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ ተልዕኮውንም ኦነግ-ሸኔ እንደተቀበለና ድምጻዊውን ኢላማ ማድረግ ለምን እንዳስፈልገ በሰጠው ቃል መግለጹን ተናግረዋል።

የግድያ ተልዕኮውን እንዲፈጽም ከሸኔ ቡድን በሰኔ ወር ውስጥ ሦስት ጊዜ ተገናኝተው እንዳሳመኑትና በመጀመሪያ ላይ ግድያው የሚፈጸምበት ግለሰብ ሃጫሉ መሆኑን እንዳልተነገረው ነገር ግን የተለያዩ የግድያ ኢላማ የሆኑ ሰዎች እንዳሉ እንደተነገረው ጠቅሰዋል።

ግድያውንም መፈጸም አስፈላጊ የሆነው "መንግሥት በመዳከሙና ይህ ካልተፈጸመ የኦሮሞ ሕዝብ አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል" በመግለጽ ለእራሱም ድርጊቱ ጥቅም እንደሚያስገኝለት ጥላሁን ያሚ ለፖሊስ በሰጠው ቃል ማመኑን ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።

ከግድያው ጀርባ ሌሎች ቡድኖች ሊኖሩበት ስለሚችሉና የተደራጀና ሰፋ ያለ ትስስር ያለው በመሆኑ ምርመራው እንደሚቀጥልና ዘርዝር ሁኔታዎች በቀጣይነት ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

በግድያው ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳላቸው ከተነገረው ግለሰቦች መካከል ጥላሁን ያሚና አብዲ አለማየሁ እንደተያዙ የተገለጸ ሲሆን ሦስተኛ ተጠርጣሪ ከበደ ገመቹ ግን አለመያዙ ተነግሯል።

ከዐቃቤ ሕግ የቀረበው መረጃ እንደሚያመለክተው ከድምጻዊው ግድያ ጋር የቀጥታ ተሳትፎ ያላቸው ሦስቱ ግለሰቦች መለየታቸውን አመልክቶ የድርጊቱ አቀናባሪና አስፈጻሚ ደግሞ ኦነግ-ሸኔ የተባለው ቡድን መሆኑን ከተጠርጣሪዎቹ መታወቁ ተገልጿል።

ሰኔ 22 ምሽት አዲስ አበባ ውስጥ በጥይት ተመትቶ የተገደለው የታዋቂው ድምጻዊ የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በመላ አገሪቱ ድንጋጤን የፈጠረ ሲሆን ግድያውን ተከትሎም በአዲስ አበባ ከተማና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተፈጠረ አለመረጋጋት ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወቃል።

ግድያውን ተከትሎ በድርጊቱ የተጠረጠሩ ከአስር በላይ ሰዎች በፖሊስ ተይዘው ምርምራ እየተደረገባቸው እንደሆነ አቃቤ ሕግ ተገልጾ ነበር።