ከሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል በኋላ በአርሲ ዞን የተከሰተው ምንድን ነው?

ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም ምሽት ባልታወቁ ሰዎች በጥይት ተመትቶ ህይወቱ ማለፉ ከተሰማ በኋላ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችና በአዲስ አበባ ውስጥ ግጭቶች ተስተውለዋል።
በእነዚህ ግጭቶች የሰው ህይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት መድረሱን የመንግሥት ባለስልጣናት ይናገራሉ። ከእነዚህም መካከል አርሲ ዞን በደረሰ ጥቃት 23 ሰዎች ህይወት ማለፉንና በርካታ ንብረት መውደሙን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አልዩ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የአርሲ ዞን 28 ወረዳ እንዳሉት የሚናገሩት አስተዳዳሪው ችግሩ የተስተዋለው በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች ሳይሆን በአምስቱ ብቻ መሆኑን ይገልጻሉ።
ከሞቱት ሰዎች መካከል አንድ የፓሊስ እና አንድ የሚሊሻ አባል እንደሚገኙበት ገልፀው፣ ግጭቱ የተከሰተባቸውን ቦታዎችን በስም ሲጠቅሱ ዶዶታ፣ ዝዋይ ዱግዳ፣ ጢዮ፣ መልካና ጀጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የዞኑ አስተዳዳሪ ግጭቶች የተከሰቱት በሰዎች መካከል በነበረ ጠብ እንጂ የብሔርም ሆነ የሃይማኖትም መልክ አልነበረውም ብለው ለቢቢሲ ቢናገሩም ጥቃቱ የደረሰባቸው ሰዎች ግን በሐይማኖታቸውና በማንነታቸው ምክንያት በደል እንደተፈፀመባቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ችግሩ ባጋጠመባቸው የተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚኖሩ ሰዎችን ቢያናግርም አንዳንዶቹ ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሲሆን፤ ሌሎች ግን በሪፖርቱ ውስጥ ስማቸው እንዲጠቀስ ፈቃደኛ ቢሆኑም ቢቢሲ ያሉበትን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ዘገባውን ያለስማቸው አውጥቷል።

ቀርሳ
ሦስት የቤተሰቦቻቸውን አባላት ደረሰባቸው ባሉት ጥቃት አጥተዋል። "የአክስቴን ልጅ፣ ልጁንና አማቹ ተገድለዋል" ሲሉ ለቢቢሲ በሃዘን ይናገራሉ።
የከፋ ችግር የነበረው በአርሲ ዞን በቀርሳ ሙኔሳ ወረዳ ነበር ያሉት ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰብ የደረሰውን ሲገልፁም፤ ሙኔሳ ዳሞት ቅምቢባ የሚባል ገበሬ ማኅበር የጥቃቱ እምብርት ነው ይላሉ።
በአካባቢው የሚገኝ ወደ 40 ገበሬ ማኅበር ላይ ጥቃቱ እንደደረሰ መረጃ አለን የሚሉት እኚህ ግለሰብ ግድያና ዘረፋ የተካሄደው ዳሞት ቅምቢባ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ነው ብለዋል።
ጥቃቱ የደረሰው ድምጻዊ ሃጫሉ መገደሉ በተሰማበት ሰኞ ሌሊት መሆኑን የሚገልፁት እኚህ ግለሰብ ጥቃት አድራሾቹ የታጠቁ እንደነበሩ ይናገራሉ።
"ፊታቸውን ሸፍነው ነበር፤ የሚፈልጉትን ሰው በስም እየጠሩ በሩን እያንኳኩ ነበር የሚያስወጡት" በማለትም ገጀራ፣ ስለት ያላቸው ነገሮችና ጦር መሳሪያ መያዛቸውን ያስረዳሉ።
በዚህ አካባቢ ሦባት ሰዎች በገጀራና በጥይት መገደላቸውን በመግለጽ ሁለት ሰዎች ከባድ መቁሰል ጉዳት ደርሶባቸው በአሰላ ሆስፒታል እንደሚገኙ ነግረውናል።
"ሁለት ሰዎች (ስማቸውን ጠቅሰዋል) ሞተዋል ብለው ጥለዋቸው ሄደው ነው በህይወት የተገኙት" በማለት በአሁኑ ሰአት በአሰላ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እያገኙ መሆኑን ገልፀዋል።
በማግስቱ ማክሰኞ ረፋድ ላይ ፖሊስ መምጣቱንና የሞቱና የቆሰሉትን ሰብስቦና ማኅበረሰቡን አረጋግቶ መሄዱን ያስታውሳሉ። ነገር ግን በስፍራው የፖሊስ ኃይል አለመኖሩን በመገንዘባቸው ጥቃት አድራሾቹ በድጋሚ መምጣታቸውን የሚናገሩት እኚህ ግለሰቡ የአካባቢው ሰው ሸሽቶ ሙኔሳ ገብርኤል ወደሚባል አካባቢ ሄዶ ማደሩን ገልፀዋል።
በዚህ ዕለትም ንብረቶች መዘረፋቸውን ቤቶች መቃጠላቸውን የሚናገሩት ግለሰቡ በማግስቱ ረቡዕም፣ የሞቱት ሰባት ሰዎች ቀብር መከናወኑን ይገልፃሉ።
ፖሊሶች በወቅቱ መጥተው የነበረ ቢሆንም ሁኔታዎች የተረጋጉ ሲመስሉ "ዳግም አይመጡም" ብለዋቸው መሄዳቸውን ያስታውሳሉ።
ነገር ግን ለሦስተኛ ጊዜ ጥቃት አድራሾቹ በመምጣታቸው ለለቅሶ ተሰባስቦ የነበረው ሰው ነፍሱን ለማትረፍ በየጫካው ማደሩን ይገልፃሉ።
ከቅዳሜ ጀምሮ ፖሊስ በአካባቢው በቋሚነት ተመድቦ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ ቤት ንብረታቸውን ጥለው የሸሹ ሰዎችን በግዴታ የአካባቢው አስተዳደርና ፖሊስ እያስመለሳቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
በአካባቢው እንዲህ አይነት ነገር ሲደርስ የመጀመሪያው ነው የሚሉት ግለሰቡ፤ ከዚህ በፊት የተለያዩ አለመረጋጋቶች በአገሪቱ ውስጥ ሲከሰቱ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት የሚከሰት ቢሆንም እንደ አሁኑ ግን በሐይማኖት ላይ ብቻ ያነጣጠረ ጥቃት አይተው እንደማያውቁ ገልፀዋል።
በአካባቢው የደረሰው የብሔር ግጭት አይደለም የሚሉበትንም ምክንያት ሲያስረዱ ቤታቸው የወደመባቸው፣ የሞቱ የተዘረፉ ሰዎች በአካባቢው የሚኖሩ የተለያዩ ብሔር ሰዎች ነገር ግን የአንድ እምነት ተከታዮች መሆናቸውን በመጥቀስ ነው።
ዴራ
በአርሲ ዴራ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና ልጃቸውን ያጡት ግለሰብ ልጃቸው ከአዳማ ሊጠይቃቸው የመጣው ሰኞ ዕለት ማታ እንደሆነ ይናገራሉ።
ሰኞ ለማክሰኞ አጥብያ የሃጫሉን ሞት ተከትሎ በአካባቢያቸው ረብሻ መከሰቱን ተናግረዋል። ልጃቸው በአጥር ዘሎ ወደ ጎረቤት ጊቢ ሲያመልጥ ከዚያ ጎትተው በማውጣት መንገድ ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
400 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ቤታቸው፣ እስከነ ሰርቪሱ፣ ሱቃቸው እስከነ ሙሉ እቃው መዘረፍ መቃጠሉን እንዲሁም ከብቶቻቸውን መንዳታቸውን ይናገራሉ።
ሌላኛው ልጃቸው መፈንከትና ስብራት እንደደረሰበት ገልጸዋል።
ግለሰቡ የሚሉት በከተማዋ ላይ በደረሰው የቤት ቃጠሎ ወደ 300 የሚደርሱ ቤቶች መውደማቸውን ገልፀው። በአሁኑ ሰዓት ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ይናገራሉ።
በከተማዋ የጸጥታ ኃይል ቢኖርም፣ ከአሰተዳደሩ ምንም ዓይነት መፍትሄ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።
በአካባቢው በሚገኝ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት ከ50 በላይ ሰዎች እንደሚገኙ የሚናገሩት ቢቢሲ ያናገራቸው ግለሰቦች፣ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ በሚገኝ አዳራሽና በየመቃብር ቤት በረንዳ ላይ ተጠልለው እንደሚገኙ በመግለጽ ማንም የሚመለከተን አካል አልመጣም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል።
በአካባቢው የደረሰው ጥቃት የሐይማኖት መልክ እንደነበረውም በመግለጽ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን በሐይማኖታቸው ምክንያት ጥቃት እንደደረሰባቸው ይናገራሉ።
ምግብ ቤት፣ ወፍጮ ቤት፣ ሆቴል፣ ሥጋ ቤት፣ የዱቄት ፋብሪካ፣ መጋዘን፣ እንጨት ቤቶች መቃጠላቸውን ያነጋገርናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል።
በየጥሻው ውስጥ ተደብቀን ነው የተረፍነው የሚሉት ግለሰቦቹ፤ ጥቃቱ አድራሾቹ ስለት ያላቸው መሳሪያዎች፣ ጦር መሳሪያዎች ይዘው እንደነበር ተናግረዋል።
ልጆቻቸውን በየዘመዱ የበተኑ፣ አልባሳት እና ምግብ የሌላቸው ሰዎች በቤተክርስቲያኒቱና በአካባቢው ሕዝብ እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ይናገራሉ።
በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ከተጠለሉ ስድስተኛ ቀናቸው እንደሆነ የሚናገሩት ግለሰቦቹ ከአካባቢው አስተዳደር ብቅ ብሎ እንኳን የጠየቀን የለም ሲሉ ለቢቢሲ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
አዳማ ውስጥ የመንግሥት ሠራተኛ የነበረውን ሊጠይቃቸው የመጣ ልጃቸው በአጥቂዎቹ የተገደለባቸው አባት ሐዘን የሚቀመጡበት ቦታ አጥተው በሐዘን ክፉኛ መጠቃታቸውን ለመግለጽ "ምነው ልጄ እኔን ብሎ ባለመጣ" በማለት እራሳቸውን በጥፋተኝነት ስሜት እየወቀሱ ነው።
አርሲ ነገሌ
ቢቢሲ ያነጋገራት በአርሲ ነገሌ የንግድና የመኖሪያ ቤት ያላት የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ግለሰብ ሌላው ማክሰኞ ዕለት በከተማዋ በተፈጸመው ጥቃት ባለቤቷንና ንብረቷን አጥታለች።
እርሷ እንደምትለው የሃጫሉ ሞት ከተሰማ በኋላ ለሊቱን ከርቀት ጩኸት ይሰማቸው ነበር። በቅድሚያ የሞተ ሰው ያለ መስሎን ወጥተን አየን ስትል ሁኔታውን ታስታውሳለች።
መኖሪያቸው የሚገኘው አርሲ ነገሌ ባለ ቀበሌ ውስጥ መሆኑን ትናገራለች። በዚህ አካባቢ አስር ክፍል መኝታ ቤት (ቤርጎ) ያለው ግሮሰሪ እንደነበራት እንዲሁም ቤታቸው ከግሮሰሪው ጀርባ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጻለች።
"ግለሰቧ በፊትም ይዝቱ የነበሩ ሰዎች አሉ" ትላለች። ስለዚህ በከተማዋ ውስጥ ጥቃቱ ሲፈጸም እርሷም ሆነች ባለቤቷ ቤታቸውን ዘግተው ከተቀመጡ አደጋው ወደ እነርሱ እንደማይመጣ አስበው ነበር።
"ባለቤቴ 'ቤት ውስጥ ከተቀመጥን የሚነካን የለም' ሲለን ዘግተን ተቀመጥን፤ እነርሱ ግን ሆ ብለው በሩን ሰባብረው ገቡ" ትላለች።
በጥቃቱ በንግድ ቤታቸው ውስጥ የሚሰሩ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም በራቸው ላይ ደግሞ 'ለምን ይህንን ታደርጋላችሁ?' ያለ ጎረቤት መገደሉን ታስታውሳለች።
እርሷ፣ ልጆቿንና ሠራተኞቿ ጎረቤት ያስጥለናል ብለው በአጥር ሾልከው ቢሸሸጉም ጥቃት አድራሾቹ እዚያም ተከታትለው መጥተው እንደወሰዷት ትናገራለች።
በዚህ ወቅትም ይፈልጉ የነበሩት ባለቤቷን እንደነበር በመናገር እየጎተቱ እንደወሰዷት እንደምታስታውስ ለቢቢሲ ተናግራለች።
ህይወቷ የተረፈው በቀበሌው አስተዳደር አካባቢ የሚገኙ የፀጥታ አካላት አማካኝነት መሆኑን በመግለጽ፣ የጸጥታ አባላቱም ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷት ገልጻለች።
የባለቤቷን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል የሰማችው በወሬ መሆኑን የምትናገረው ይህች ግለሰብ በአሁኑ ሰዓት በሰው ቤት ተጠልላ በስጋት እንደምትኖር ትናገራለች።
የባለቤቷ አስከሬንም ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ አድሮ በነጋታው መቀበሩንም ለቢቢሲ አረጋግጣለች።
"አሁንም ዛቻ አለ" የምትለው ይህች እናት "ሲያስፈራሩን ሰው ቤት ህጻናት ይዤ በፍርሃት ነው ያለሁት" በማለት ቤት ንብረቷ እንዲሁም የልጆቿ አባትን አጥታ መሄጃው እንደጠፋት ለቢቢሲ ገልጻለች።
በከተማዋ አምስት ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የምትናገረዋ ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ጥቃቱ የሐይማኖት ብቻ ሳይሆን የብሔር መልክም ነበረው ትላለች።
በከተማዋ ተዉ ስላሉ የተገደሉ፣ የተወጉ፣ የተደበደቡ ሰዎች አሉ የምትለው ግለሰቧ ከዚህ የባሰ የደረሰም አለ በማለት የሰማችውን ለቢቢሲ አካፍላለች።
ግለሰቧ አክላም "ሕጻናት ባዩት ነገር አእምሯቸው ተረብሿል፤ የ11 ዓመት ልጅ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለውን ግለሰብ በማየቱ ራሱን አጥፍቷል" ስትል ለቢቢሲ ያለውን መረበሽና ጭንቀት ታስረዳለች።
ህጻናቱ በፍርሃት ነው ያሉት በማለትም፣ ወደ ከተማዋ የጸጥታ ኃይል ማክሰኞ ከሰዓት ገብቶ ቢያድርም ጥቃት አድራሾቹ በነጋታው ወደ ገጠር ቀበሌዎች በመሄድ ጥቃት ማድረሳቸውን ተናግራለች።።
የአርሲ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ጀማል የደረሰውን የንብረት ውድመት ለማጣራት በአካባቢው ፖሊስ መምሪያ የሚመራ ኮሚቴ መዋቀሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አጠቃላይ ጉዳት
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነት ግርማ ገላን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ውስጥም በተፈጠረው አለመረጋጋት 11 የጸጥታ ኃይሎችን ጨምሮ የ156 ሰዎች ህይወት አልፏል። ከዚህ በተጨማሪ በተፈጸሙት ጥቃቶች ሳቢያ 167 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
ምክትል የፖሊስ ኮሚሽነሩ ጨምረውም የተፈጸሙትን ጥቃቶች "ዘግናኝና አሳፋሪ የግድያ ወንጀሎች" መሆናቸውን አመልክተው የዚህ ድርጊት አላማ በማኅበረሰቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር ታስቦ የተፈጸመ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በተለያዩ ስፍራዎች በተፈጸመው ጥቃቶች ከደረሰው ጉዳትና የንብረት ውድመት ጋር በተያያዘም ፖሊስ ጠርጥሬያቸዋለሁ ያላቸውን ግለሰቦች መያዙን አስታውቋል። 1084 ሰዎችን መያዙን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ሲያስታውቀ፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋም በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።

















