በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በደረሰ ጥቃት ሰዎች መጎዳታቸው ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, AMMA
ሸኔ የተባለው ታጣቂ ቡድን ከሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተቀናጀ በአማራ ክልል ውስጥ ጥቃት መፈጸሙን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ መግለጻቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘገቡ።
በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ውስጥ በሚገኝ ደዌ አረዋ ወረዳ ላይና በባቲ ከተማ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ወቅት በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የቡድኑ መሪ መገደሉንና ሌሎች በጥቃቱ ተሳታፊ የነበሩ ታጣቂዎች ከነመሳሪያቸው መያዛቸውም በዚሁ ዘገባ ላይ ተገልጿል።
ርዕሰ መስተዳደሩ ጨምረውም በባቲ ከተማ ውስጥ በአንድ ሆቴል ላይ በተፈጸመ የቦንብ ጥቃት አምስት ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን ገልጸዋል።
አቶ ተመስገን እንዳሉት ጥቃቱ በአዲስ አበባ ከተፈጸመው የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በአካባቢው ሽብር ለመፍጠር በማቀድ የተፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።
በብሔራዊው ቴሌቪዥን ላይ በቀረበው ዘገባ እንደታየው በእሳት የወደሙ ቤቶችና አንድ አውቶብስ ከደረሰበት ጥቃት መቃጠሉ ይታያል።
አቶ ተመስገን የታጣቂ ቡድኑ ዓላማ አዲስ አበባ ከተፈፀመው ግድያ ር የተያያዘ ተልእኮ እንደተሰጣቸው አረጋግጠናል ብለዋል።
ከታጣቂ ቡድኑ ጋር በነበረው የተኩስ ልውውጥ አንድ የጸጥታ አባል መቁሰሉን አቶ ተመስገን በሰጡት መግለጫ ላይ ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከዚህ በኋላ መንግሥት "የሸረሪቱ ድር ላይ ብቻ ሳይሆን ሸረረቷ ላይም አተኩሮ ይሰራል" ብለዋል።
አክለውም ክልላቸው በየትኛውም መልኩ ከፌደራል መንግሥት ጎን እንደሚቆሙ ተናግረዋል።
ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በተፈጠረ ግርግር ፖለቲከኞች ጋዜጠኞችና የተለየዩ ከተማ ነዋሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል።
እንዲሁም በአዲስ አበባ በደረሱ ጥቃቶች ሁለት ፖሊሶችን ጨምሮ ቢያንስ አስር ሰዎች ህይወታቸው መጥፋቱ የተገለጸ ሲሆን በተመሳሳይ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ውስጥም 11 የጸጥታ ኃይሎችን ጨምሮ 156 ሰዎች ሞተዋል።
ከማክሰኞ ጀምሮ በነበሩት ተከታታይ ቀናት በኦሮምያ በተፈጸሙ ግድያዎችና የንብረት ውድመቶች የተጠረጠሩ 1084 ሰዎችን መያዙን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ሲያስታውቀ፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋም በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።












