ፋና ብሮድካስቲንግ የመቀሌ ኤፍ ኤም ስርጭቱን አቋረጠ

ፋና

የፎቶው ባለመብት, FBC

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ከትግራይ ክልል መቀለ ከተማ በኤፍኤም አማካይነት ሲያደርገው የነበረውን ስርጭቱን ማቋረጡን የቢቢሲ ሪፖርተር አረጋገጠ።

የቢቢሲ ሪፖርተር የብሮድካስት ባለስልጣን ለጣብያው የጻፈውን ደብዳቤ ከድርጅቱ ጋዜጠኞች በማየት ማረጋገጥ እንደቻለው ስርጭቱ ከትናንት ጀምሮ እንደተቋረጠ የተገለፀ ሲሆን ቢሮውም መዘጋቱን ለማወቅ ተችሏል።

ቢቢሲ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የመቀለ ቅርንጫፍ ጋዜጠኛ ከሆነው ዮናታን ገዛኸኝን ባገኘው መረጃ መሰረት አራት የድርጅቱ ሠራተኞች ከአርብ እለት ጀምሮ ከደሞዝ እና ከሥራ መታገዳቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሷቸዋል።

መገናኛ ብዙሃኑ የመቀለ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ከዚህ ቀደም በተከሰተ አለመግባባት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ይታወሳል።

ቢቢሲ ከፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት ቅርጫፎች ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገመዳ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ለማግኘት በስልክ ባደረገው ጥረት ከድርጅቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ምላሽ እንደሚሰጡንና ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ እንድንደውል ቢነግሩንም በተደጋጋሚ ያደረግነው የስልክ ጥሪ ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የመቀለ ቅርንጫፍ 32 ሠራተኞች የነበሩት ሲሆን የሠራተኞቹ መብትና ሌሎች የሚነሱ ጥያቄዎች በሂደት እንደሚመለሱ መግለፁን ከጣቢያ ባልደረቦች ለማወቅ ችለናል።

ለቅርንጫፍ የሬዲዮ ጣቢያው በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በኩል የተጻፈውን ደብዳቤ በተመለከተም በስልክ መረጃ ለማግኘት ባለስልጣኑ ጋር ያደረግነውም ሙከራ ስልካችን ባለመነሳቱ አልተሳካም።

ቢቢሲ በማንኛውም ሰዓት ከሁለቱም ወገኖች ምላሽ ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት የሚቀጥል ሲሆን ጉዳዩን በሚመለከት ከሚመለከታቸው አካላት የምናገኘውን ተጨማሪ መረጃ እናቀርባልን።