አወዛጋቢው አያ ሶፊያ ቅርስ ዛሬ ለጁምአ ጸሎት ክፍት ይሆናል

አያ ሶፊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

1ሺ 500 ዓመት ዕድሜ ያለው ዝነኛው የአያ ሶፊያ ቅርስ መስጊድ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።

ድሮ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የነበረው አያ ሶፊያ አሁን መስጊድ ሆኗል፡፡ ቱርክም ሆነች መላው ዓለም የሚደመምበት የአያ ሶፊያ ሕንጻ በከፊል መስጊድ ሆኖ እንዲያገለግል የወሰነው ፍርድ ቤት ነው፡፡

በቱርክ ኢስታንቡል የሚገኘው አያ ሶፊያ ከዓለም ቅርሶች ልዩ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡

ሙስሊሞች በዜናው ተደስተዋል፤ ጁምዓ ሁሉም ሰው እዚያ ለመገኘት ይፈልጋል ብለዋል የኢስታንቡል ከንቲባ የርሊካያ አሊ፡፡

አንድ ሺ አምስት መቶ ዓመት ያስቆጠረው ይህ በዩኔስኮ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ታሪካዊ ሕንጻ ወደ ሙዚየምነት የተቀየረው በፈረንጆቹ በ1934 ነበር፡፡ ከዚያ ቀደም ባሉ ረዥም ዓመታት ግን መስጊድ ነበር፡፡

ይህንን ቅርስ ወደ መስጊድነት እንዲመለስ መወሰኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ ይህም የሆነው ቅርሱ በቢዛንታይን ጊዜ ሲገነባ የዓለም ትልቁ ቤተ ክርስቲያን የነበረ በመሆኑ ነው፡፡

ከዛሬ አርብ ጀምሮ በአንድ ጊዜ አንድ ሺ ሰዎች በአያ ሶፊያ ተገኝተው ሊሰግዱበት ይችላሉ ተብሏል፡፡

የቱርኩ መሪ ጣይብ ኤርዶጋን ዛሬ ለጁምአ ከሚገኙት ምዕመናን መካከል አንዱ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡

ይህ ቅርስ መስጊድ ይሁን ወይስ ቅርስ ሆኖ ይቀጥል የሚለው ጉዳይ ላይ ለዓመታት የቱርክ ማኅበረሰብን ሲያነታረክ ነበር፡፡

ኤርዶጋን ይህ ቅርስ መስጊድ እንዲሆን መወሰኑን ሲያሳውቁ በርካቶች የተደሰቱትን ያህል ከፍተኛ ቅሬታዎችም ተስተናግደዋል፡፡

ለምሳሌ የካቶሊኩ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ‹‹ለኢስታንቡል እጸልያለሁ፤ ሳንታ ሶፊያን ባሰብኩ ቁጥር ሐዘኔ ይበረታል›› ብለዋል ውሳኔውን ተከትሎ፡፡

የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትም በውሳኔው ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

ፓትሪያርክ ባርቶሎሜ እንደተናገሩት ይህ ቅርስ መስጊድ መሆኑ የብዙ ኦርቶዶክሶችን ልብ የሚሰብር ነው፡፡

350 ቤተክስትያኖችን ያቀፈው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ በበኩሉ ውሳኔው እንዲቀለበስ ጠይቋል፡፡ ይህ ውሳኔ አንድነትን ሳይሆን ክፍፍልን የሚፈጥር ነው ሲሉ አስጠንቅቋል፡፡

‹‹ኤርዶጋን ግን ሉአላዊ አገር ነን፡፡ ውሳኔያችንም ሉአላዊነታችንን የሚያረጋግጥ ነው›› ብለዋል፡፡

በሕንጻው ውስጥ የሚገኙ የቅድስት ማርያምና ሌሎች ክርስቲያናዊ ምሥሎችና ምልክቶችም ተጠብቀው እንደሚቆዩ አረጋግጠዋል፡፡

‹‹አያ ሶፊያ ከ86 ዓመታት በኋላ ወደ መስጊድነት ተቀይሯል፡፡ የኢስታንቡል ወራሪ የነበረው የሕንጻው ባለቤት በኑዛዜው ቤቴ መስጊድ እንዲሆን ባለው መሰረት ኑዛዜው እነሆ ተከብሮለታል›› ብለዋል ኤርዶጋን፡፡

ሆኖም ኤርዶጋን ሕንጻው ለክርስቲያኖችም ክፍት መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ከክርስቲያች በተጨማሪም ለጎብኚዎች ዓመቱን ሙሉ ክፍት ይደረጋል፡፡

ያ ሶፊያ የማን ነው?

አያ ሶፊያ በ537 በቢዛንታይን ኢምፐረር ጀስቲኒያን የተገነባ ልዩና ብርቅዬ ቤተክርስቲያን ነበር፡፡ ንጉሡ ይህ ስፍራ ትልቁ የዓለም ቤተ ክርስቲያን እንዲሆን አስቦ እንዳስገነባው ይነገራል፡፡

ሆኖም እንደ አውሮጳዊያኑ በ1453 ኦቶማን ሱልጣን አሕመድ ዳግማዊ ቀድሞ ኮንስታንቲኖፕል ትባል የነበረችውን ኢስታንቡልን በመውረር ተቆጣጠረ፡፡

ወረራውን ተከትሎም የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ካቴድራል የነበረችው አያ ሶፊያ ወደ መስጊድነት ተቀየረች፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ መስጊድነት በመቀየሩ ረገድ በዚያ ዘመን አራት ሚናሬቶችም እላዩ ላይ እንዲገነቡ ተደርጓል፡፡

አያ ሶፊያ ለብዙ መቶ ዓመታት መስጊድ ሆኖ ካገለገለ በኋላ ይህ ስፍራ በከማል አታቱርክ ግፊት ወደ ሙዝየምነት ተቀየረ፡። አያ ሶፊያን በዓመት ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ቱሪስቶች ይጎበኙታል፡፡