ፌስቡክ አፍሪካ ውስጥ ርካሽ የኢንተርኔት አገልግሎት ሊያቀርብ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ግዙፍ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ የሆነው ፌስቡክ በአፍሪካ ውስጥ የኢንተርኔት ትስስርን ለማሻሻል በሚያፈሰው መዋዕለ ነዋይ የአህጉሪቱ ምጣኔ ሃብት እድገት ላይ አስተዋጽኦ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
የኢንተርኔት ትስስር ላይ በሚደረገው ለውጥ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ በአህጉሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ወደ 60 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ እድገትን ያመጣል ተብሏል።
ፌስቡክ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የኢንተርኔት ተደራሽነት በጨመረ ቁጥር በአህጉሪቱ የሚኖረው የኢንተርኔት ዋጋ ላይ ከፍተኛ ቅናሽ እንደሚኖረው ገልጿል።
ፌስቡክ በአፍሪካ ውስጥ በሚመድበው መዋዕለ ነዋይ የኢንትርኔት ዳታ ማዕከላት፣ የባሕር ውስጥ ማስተላለፊያ ገመዶችና የዋይ ፋይ መሰረተልማቶችን በመዘርጋት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎች የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አቅዷል።
እንዲሁም በኢንተርኔት አማካይነት የሚደረጉ የንግድ ልውውጦችንና የሥራ ማመልከቻዎችን ለማበረታታትም ያግዛል ተብሏል።
አስካሁንም ፌስቡክ በሰባት አገራት ውስጥ የዋይፋይ አገልግሎትን የጀመረ ሲሆን በኡጋንዳና በናይጄሪያ ደግሞ የ3ጂ ሽፋንን አስፋፍቷል።
ከሰሃራ በታች ባለው የአፍሪካ ክፍል ውስጥ ከሚገኘው ሕዝብ ከግምሽ የሚበልጡት የኢንተርኔት አገልግሎትን አያገኙም። በተጨማሪም በአገራቱ ውስጥ ያለው አገልግሎት ከሌላው ዓለም ጋር ሲወዳደር ውድ ነው።
በርካሽ ኢንተርኔት አቅርቦት ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ለአንድ ሚጋ ባይት የኢንትርኔት አገልግሎት የሚወጣው ወጪ ከአማካይ ገቢ 8 በመቶን የሚጠይቅ ሲሆን በአሜሪካ 2.7 በመቶ በአስያ ደግሞ 1.5 በመቶ ብቻ ነው።
በአፍሪካ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው የኢንተርኔት ግልጋሎት የሚውለው የፌስቡክ መተግበሪያዎች የሆኑትን ኢንስታግራምና ዋትስአፕን ለመጠቀም ነው።
ዋነኛው የማኅበራዊ መገናኛ መድረክ የሆነው ፌስቡክ እንዳስታወቀው ከሁለት ዓመት በፊት አፍሪካ ውስጥ 139 ሚሊዮን ሰዎች አገልግሎቶቹን ይጠቀማሉ።
















