ለሳምንታት የተቋረጠው ኢንተርኔት አገልግሎት ተመለሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ከሦስት ሳምንታት በላይ ተዘግቶ የቆየው የሞባይል ኢንትርኔት አግልግሎት መመለሱ ተነገረ።
የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተከሰተው አለመረጋጋት ሳቢያ የኢትዮጵያ መንግሥት የመደበኛና የሞባይል ኢንትርኔት አገልግሎቶችን በመላዋ አገሪቱ እንዲቋረጥ አድርጎ መቆየቱ ይታወሳል።
ቢቢሲ ዛሬ ረፋድ ከአዲስ አበባ ባሻገር ወደተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በመደወል ከነዋሪዎች ለማጣራት እንደሞከረው የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ነገር ግን አገልግሎቱ በመላው አገሪቱ እንደተመለሰ ለማረጋገጥ አልቻለም።
ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ የዋይፋይ የኢንተርኔት አገልግሎት መመለሱ ይታወቃል። በርካታ ተጠቃሚ ያለው የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ደግሞ ዛሬ ሐሙስ በበርካታ ስፍራዎች ላይ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ እንደዋነኛ ምክንያት የጠቀሰው አንዳንድ ወገኖች ግጭትና አለመረጋጋትን የሚያባብሱ የጥላቻ መልዕክቶችን ለማሰራጨት እየተጠቀሙበት መሆኑን ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የሆኑት ቢልለኔ ስዩም በወቅቱ ለቢቢሲ እንዳሉት የኢንተርኔት አገልግሎት የብሔር ጥላቻን ለማስፋፋት ጥቅም ላይ በመዋሉ መንግሥት አገሪቱንና ሕዝቡን የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት ለማቋረጥ መገደዱን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ዛዲግ አብረሃ በበኩላቸው ኢንተርኔት በአንዳንድ ወገኖች ለጥላቻ ንግግር ማሰራጫ መሳሪያ እንደተደረገ ጠቅሰዋል፤ በብሔሮችና በሐይማኖቶች መካከል ግጭቶች እንዲቀሰቀስ መሳሪያ በመሆኑ እንዲቋረጥ መደረጉን አመልክተዋል።
ጨምረውም "መምረጥ የነበረብን ከመረጃ ነጻ ፍሰትንና የሕዝባችን ህይወት ከመካከል ነበር፤ በዚህም ለሰው ልጅ ሕይወት ቅድሚያ ሰጥተናል" ብለው የተወሰደው እርምጃ የዜጎችን ደኅንነት ከመጠበቅ አንጻር መሆኑን አመልክተዋል።
የአገሪቱ ባለስልጣናት የኢንተርኔት አገልግሎትን በማቋረጣቸው ከተለያዩ ወገኖች ትችትና ወቀሳ ሲቀርብባቸው የሰነበተ ሲሆን፤ በምላሻቸው የነበረው አለመረጋጋት ወደነበረበት ሲመለስ የኢንተርኔት አገልግሎቱ እንደሚቀጥል ገልጸው ነበር።
እነሆ ባለፈው ሳምንት የዋይፋይ አግልግሎት ዛሬ ደግሞ የሞባይል ዳታ የኢንርተኔት አገልግሎት በበርካታ ቦታዎች ላይ ወደ ሥራ መመለሱ ተነግሯል።
የእለት ከዕለት ሥራቸው ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉ በርካታ ተቋማት ባለፉት ሦስት ሳምንታት ከፍተኛ መጠን ያለው ገቢ ማጣታቸውን እየገለጹ ነው።
ከዚህ በፊት በአገሪቱ ተቋርጦ የነበረውን የኢንተርኔት አገልግሎት በማስመልከት 'ኔትብሎክስ' የተሰኘው የኢንተርኔት አገልግሎት ጥናት ቡድን ለቢቢሲ እንደተናገረው በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት አገሪቱ በቀን በትንሹ 4.5 ሚሊየን ዶላር ታጣለች ይህ የገንዘብ መጠን ዝቅተኛው ግምት እንደሆነም ተገልጿል።
ከዚህ አንጻር ባለፉት ሳምንታት ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ መጠን የሚታጣ ሲሆን ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉ በርካታ ሥራዎች መስተጓጎል እንደገጠማቸው ይገመታል።
ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ በመላው አገሪቱና በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ሰበብ ከ10 ጊዜ በላይ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ይታወሳል።














