ነፍሰ ጡር እናቶች ለምን የተለያየ ምግብ ያምራቸዋል?

ቡና የያዘች ነፍሰጡር ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የምግብ አምሮት በእርግዝና ወቅት በርካታ እናቶች ላይ ይስተዋላል

ፍርፍር አማረኝ፣ ቆጮ አማረኝ፣ ጭኮ አማረኝ፣ ጥህሎ አማረኝ፣ ቸኮሌት አማረኝ. . .የሚሉና የመሳሰሉ ምግቦችን ብዙ ነፍሰ ጡሮች አማረን ሲሉ እንሰማለን።

በተለምዶ፤ በእርግዝና ወቅት ለእናት ወይም ለልጅ የሚያስፈልገው ምግብ ሴቶችን እንደሚያምራቸው ይነገራል።

እርግዝና ረዥም፣ አድካሚ፣ አንዳንዴም ምቾት የሚነሳ የተፈጥሮ ሂደት ነው። በዚህ ወቅት ነፍሰ ጡሮች የተለያየ አይነት ምግብ ለምን እንደሚያምራቸው ሳይንስ ምን እንደሚል እንመልከት እስኪ።

አምሮት ከምን ይመጫል?

ሁሉም ነፍሰ ጡሮች አምሮት ይገጥማቸዋል ማለት አይቻልም። የለንደኗ እና የአዲስ አበባዋ እናት የተለያየ ምግብ እንደሚያምራቸውም እሙን ነው።

ለምሳሌ የጃፓን ሴቶች በብዛት የሚያምራቸው ሩዝ እንደሆነ ይነገራል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ነፍሰ ጡሮች የሚያምሯቸው ምግቦች ሰውነታቸው ከሚፈልገው የተመጣጠ ምግብ ጋር አይገናኙም።

እንዲያውም አምሮት ያለባቸው ነፍሰ ጡሮች በእርግዝና ወቅት ከተለመደው በላይ ክብደታቸው ስለሚጨምር እርግዝናው የመወሳሰብ እድሉ ሰፊ ነው።

በኒው ዮርክ ዩኒቨርስቲ የሥነ ልቦና ምሁሯ ጁልያ ሆርምስ እንደምትለው፤ አሜሪካ ውስጥ 50 በመቶ ሴቶች የወር አበባቸው ከመምጣቱ አስቀድሞ ቸኮሌት ያምራቸዋል።

የቸኮሌት አምሮት የሚከሰተው ቸኮሌት በውስጡ ለወር አበባ የሚያስፈልግ ይዘት ያለው ምግብ ስለሆነ ነው? ወይስ አምሮቱን የሚፈጥረው የሆርሞን ለውጥ ነው? በሚለው ዙሪያ ተመራማሪዎች ጥናት ሠርተዋል።

በአንድ ሙከራ ላይ ተመራማሪዎች ሦስት አይነት ሳጥን አዘጋጁ። አንዱ ወተት ያለው ነጭ ቸኮሌት፣ ሌላው ነጭ ቸኮሌት፣ ሦስተኛው ደግሞ የካካዎ እንክብል ይዞ ነበር።

ወተት ያለው ነጭ ቸኮሌት፤ በማንኛውም ቸኮሌት ውስጥ የሚገኝ ንጥረ ነገርን የያዘ ሲሆን፤ አፍ ውስጥ ይቀልጣል። ነጩ ቸኮሌት ለእይታ የማይማርክና ካካዎ የሌለው ነው።

በሦስተኛው ሳጥን ውስጥ የነበረው የካካዎ እንክብል፤ ቸኮሌት ውስጥ ያለው ንጥረ ነገር ቢኖረውም ቸኮሌት አይመስልም።

በምርምሩ የተሳተፉት ሴቶች አምሮት ሲፈጠርባቸው ከሳጥኖቹ ውስጥ አውጥተው እንዲመገቡ ተመራማሪዎቹ ነግረዋቸው ነበር።

ከቀረቡት አማራጮች አምሮት የሚቆርጠው ነጩ ቸኮሌት ነው። ይህ ማለት ደግሞ አምሮት የሚፈጠረው አንዳች ንጥረ ነገር ለማሟላት አይደለም ማለት ነው።

ሌላ ጥናት ደግሞ አምሮት ከሆርሞን ጋር እንደማይገናኝ ያሳያል። ጁልያ እንደምትለው፤ የወር አበባ ማየት ያቆሙ ሴቶች ቸኮሌት እንዳማራቸው ተናግረዋል።

እነዚህ ጥናቶች አምሮት ባህላዊና ሥነ ልቦናዊም መነሻ እንዳለው ይጠቁማሉ።

ቼኮሌትና የድንች ጥብስ የምትበላ ነፍሰጡር ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የምግብ አምሮት ሥነ ልቦናዊ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ

ምግብና የጥፋተኛነት ስሜት

በአሜሪካ እና በሌሎች አገራትም አንዳንድ ምግቦችን መመገብ የጥፋተኝነት ስሜት እንደሚያስከትል ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

ጁልያ እንደ ቸኮሌት እና አይብ (ቺዝ) የሚበዛባቸው ምግቦችን በምሳሌነት ትጠቅሳለች።

“ስበላቸው ቢያስደስቱኝም ባህሉ ቸኮሌት መመገብ እንደሌለብኝ ይነግረኛል” ትላለች።

አንድ ሰው የሆነ ምግብ መብላት የለብኝም ብሎ ራሱን አቅቦ ከቆየ በኋላ ምግቡን ከተመገበ ለማቆም ይቸገራል። ስለዚህም አልበላም ያለውን ምግብ ሲበላ ከመጠን ያልፋል።

ነፍሰ ጡሮች የሐኪም ምክር በመከተል ወይም ጤናማ አመጋግብ እንዲኖራቸው በሚል የተወሰኑ ምግቦችን አይወስዱም። ይህን ተከትሎም ለመቆጣጠር የሚከብድ አምሮት እንዲሁም ክብደት መጨመር ይከሰታል።

እርግዝና- የምግብ አምሮት የማይገታበት ወቅት?

በእግዝና ወቅት የምግብ አምሮቴን መግታት የለብኝም ብለው የሚያምኑ አሉ።

“ሴቶች መመገብ የሌለባቸውን ምግቦች በእርግዝናና በወር አበባ ወቅት ቢወስዱ አይከፋም የሚል እሳቤ አለ” ትላለች የሥነ ልቦና ተመራማሪዋ።

ለምሳሌ አንዲት ሴት ቸኮሌት ሲያምራት፤ ገበያ ላይ ካሉ ቸኮሌቶች ምርጡን ገዝታ በቀን የተወሰነ ቸኮሌት እንድትመገብ ትመክራለች።

በሌላ በኩል ራስን ማረሳሳትም ይቻላል። አንድን ነገር በማየት ወይም በማሽተት አምሮትም ማረሳሳት እንደሚቻል ጥናቶች ያሳያሉ።

ፒዛ የምትበላ ወጣት ነፍሰጡር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ተመስጦ

ሌላው መንገድ ተመስጦ (ሜዲቴሽን) ነው። አንድ ነገር እንዳማረን እውቅና በመስጠት አምሮቱ እንዲያልፍ ማድረግ ይቻላል።

እርግዝና ቀላል ወቅት አይደለም። ስለዚህም ነው ማኅበረሰባዊ መደጋገፍ የሚያስፈልገው።

ታንዛንያ ውስጥ ነፍሰ ጡር እናቶች ሥጋ፣ ዓሣ፣ አትክልትና ፍራፍሬም ሲያምራቸው የትዳር አጋራቸው ወይም ሌላው የቤተሰብ አባል ያቀርብላቸዋል። ይህም የማኅበራዊ ትብብር ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።

አመቺ ባልሆነ ሰዓት ቢሆንም እንኳን ቸኮሌትም ይሁን ጥህሎ፣ ቆጮም ይሁን ጭኮ ሲጠየቅ የሚያቀርብ አጋር፤ አፍቃሪነቱን እያሳየ ነው።