ኮሮናቫይረስ፡ 47 ሚሊዮን ሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ ላያገኙ ይችላሉ-የተባበሩት መንግሥታት

የፎቶው ባለመብት, JAY ARGUELLES
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በአስር ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሴቶች የእርግዝና መከላከያ ላያገኙ እንደሚችሉና በዚህም የተነሳ ያልታቀደ እርግዝና ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ሥነ ሕዝብ ፈንድ (ዩኤንኤፍፒኤ) አስታወቀ።
" በ114 ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የሚገኙ 47 ሚሊዮን ሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ ላያገኙ ይችላሉ" ይላል የድርጅቱ ሪፖርት።
" አገራት የሚጥሉት የእንቅስቃሴ ገደብ ለስድስት ወራት ከቀጠለ 7 ሚሊዮን ያልታቀደ እርግዝና ሊከሰት ይችላል፤ መሰረታዊ የጤና አገልግሎትም ይስተጓጎላል። የእንቅስቃሴ ገደቡ ለሚቀጥልበት እያንዳንዱ ሶስት ወራትም ተጨማሪ ሁለት ሚሊዮን ሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ ላይጠቀሙ ይችላሉ" ይላል ሪፖርቱ በተጨማሪ።
ይህ ደግሞ እንደ ፊሊፒንስ ባሉ ጽንስ ማቋረጥ ወንጀል በሆነባቸው እና በማህበረሰብ የጤና ማዕከላት እና የቤት ለቤት የጤና ፕሮግራሞች ላይ በሚሰጡ የወሊድ መቆጣጠሪያ አቅርቦቶች ላይ ለተደገፉ ሴቶች አሳሳቢ ነው።
"በፊሊፒንስ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ወደ 1.2 ሚሊየን ሴቶች ያልታቀደ እርግዝና ሊገጥማቸው ይችላል" ያሉት በፊሊፒንስ የተባበሩት መንግሥታት ተወካይ ዶ/ር ጆሴፍ ሲንጊህ ናቸው።
አክለውም ይህ የከፋው ግምት ሲሆን በዚህ ዓመት በተከሰተው ወረርሽኝ ምክንያት የወሊድ መቆጣጠሪያ አቅርቦት በግማሽ ከቀነሰ የሚከሰት ነው ብለዋል።
ያልታቀደ እርግዝና ከነርሶች፣ አዋላጆች እንዲሁም በድንገተኛ ጊዜ እንክብካቤ ጉድለት ጋር ተያይዞ የእናቶች ሞትን ሊያስከትል እንደሚችል ቡድኑ ጨምሮ ገልጿል።
የመድሃኒት እጥረት
" የኮንዶምና የተወሰኑ የእርግዝና መከላከያ መድሃኒቶች ክምችት እጥረት ገጥሞናል" ያሉት ደግሞ ሩትስ ኦፍ ሄልዝ የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የሚመሩት አሚና ኤቫንጀሊስታ ስዋንፖኤል ናቸው።
የእርሳቸው ቡድን የስነ ተዋልዶ አገልግሎቶችን በፑሬቶ ፕሪንቼሳ እና ገጠራማ የፊሊፒንስ መንደሮች የሚያቀርብ ሲሆን ከኮሮናወረርሽኝ መከሰት በኋላ ግን መድሃኒቶችን ለማጓጓዝ የሚያስችል የመጓጓዣ እጥረት በመፈጠሩ የክምችት እጥረት ገትሟቸዋል።
የመንግሥት ብሔራዊ የቤተሰብ ፕሮግራም ለቢቢሲ እንደተናገረው በቂ የወሊድ መቆጣጠሪያ ክምችት ቢኖረውም በሁሉም ግዛቶቹ ለማከፋፈል ግን ችግር አጋጥሞታል።
"በእግሯ አስር ኪሎሜትር ተጉዛ መጥታ አገልግሎቱን የምታገኝ ሴት አለች። አሁን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በተዘጉ መንገዶች ሳብያ በየፍተሻ ጣብያው ለሚያስቆሟት የፀጥታ ኃይሎች ወዴት እንደምትሄድና የምትሄድበትን ምክንያት ማስረዳት ይጠበቅባታል" ብለዋል ለፑሬቶ ፕሬቼሳ የጤና ቢሮ የሚሰሩት አናሊዛ ሄሬራ።
በፊሊፒንስ በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ የተነሳ በአንዳንድ አካባቢዎች ለአንድ ቤተሰብ አንድ ሰው ብቻ መንቀሳቀስ እንዲችል ፈቃድ ተሰጥቶታል።
" የመንቀሳቀሻ ፈቃዱ ወንድ ብቻ አይልም፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ወንዶች ናቸው የሚንቀሳቀሱት" ብለዋል የመንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት ኃላፊ ስዋንፖኤል።
አክለውም " በተለይ የትዳር አጋሯ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንደምትጠቀም ለማያውቅ ሴት መድሃኒቶቹን ማግኘት ፈታኝ ነው" ይላሉ።
አሁን ድረስ መድሃኒታቸውን የጨረሱ ሴቶች ተጨማሪ ማግኘት እንደሚፈልጉ ቢናገሩም መንቀሳቀሻ አጥተው መቸገራቸውን እንደሚነግሯቸው ገልፀዋል። ይህንን ችግር የበለጠ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ በቤት ውስጥ መቀመጥ ውሳኔው ወቅት የትዳር አጋር አብሮ ቤት መገኘቱ ነው
"በተለይ በተፈጥሮ መንገድ የሚከላከሉ የፊሊፒንስ ሴቶች ፈተና ይገጥማቸዋል፤ እርግዝና በሚከሰትበት ወቅት ከወሲብ መታቀብ የሚመርጡ ቢሆንም አሁን ግን የትዳር አጋሯ ቤት ውስጥ አብሮ በመዋሉ የተነሳ ይህ አዳጋች ነው" ይላሉ።
በጎርጎሳውያኑ በ2017 በፊሊፒንስ የተሰራ አንድ ጥናት ለአቅመ ሄዋን ከደረሱና ካላገቡ ሴቶች መካከል 49 በመቶ ያህሉ ምንም ዓይነት የወሊድ ቆጣጠሪያ እንደማይጠቀሙ ያሳያል። ያገቡ እና ማርገዝ ከማይፈልጉ ሴቶች መካከል ደግሞ 17 በመቶ የወሊድ መቆጣጠሪያ አይጠቀሙም።
" በፊሊፒንስ የሚገኙ ሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ የማይጠቀሙበት ዋነኛ ምክንያት የጎንዮሽ ጉዳትን በመፍራትና የፀረ ስነተዋልዶ ጤና ትምህርቶች በሚያሰራጯቸው ከእውነታ የራቁ መረጃዎች የተነሳ ነው" ይላሉ የዩኤንኤፍፒኤ ተወካይ ዶ/ር ጆሴፍ ማይክል ሲንግ።
" አብዛኛው ፊሊፒንሳዊ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ሲሆን ወግ አጥባቂ የኃይማኖት አባቶች ደግሞ በየቤተ እምነቶቹ በብዛት ይገኛሉ፤ እንዲሁም በደቡባዊ ፊሊፒንስ ደግሞ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሙስሊም የኃይማኖት አስተማሪዎች አሉ" ሲሉ ያክላሉ።
ያልታቀደ እርግዝና ሴቶች ላይ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ያደርሳል።














