ኮሮናቫይረስና ጫት ቃሚዎች

ጫት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሶማሊያ ውስጥ መካከለኛ የማነቃቃት ኃይል አለው የሚባለውን ጫት ይዘው የሚገቡ አውሮፕላኖች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሥራ አቁመዋል፤ ቃሚዎችም ግራ ገብቷቸዋል።

በቀደመው ጊዜ ዕኩለ ቀን ሲሆን ሞጋዲሹ ትበራለች። ከተሜው በጫት መሸጫ ሱቆች ይኮለኮላል። ሁሉም ይጠብቅ የነበረው ጫት ጭነው ከኬንያ የሚመጡትን አውሮፕላኖች ነው።

ቃሚዎች ጫታቸውን በብብታቸው ሸጉጠው ወደ ቤታቸው አሊያም ወደ ሥራ ካለሆነም ወደ መቃሚያ ቤት ያቀናሉ።

ጫት በከተሜው ሚራ የሚል ስም ተሰጥቶታል። ሚራ የቃመ ጨዋታ ያውቃል፣ ቤት ያሞቃል። ንግድ የሚጦፈው በሚራ ነው፣ ክርክር የሚደራውም እንዲሁ።

አሁን ግን ይህ ትዝታ ሆኗል። የሶማሊያ መንግሥት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከወርሃ መጋቢት ጀምሮ አንድም አውሮፕላን ድርሽ እንዳይልብኝ ብሏል፤ ምሳ ሰዓት ጠብቀው ብቅ የሚሉትን የጭነት አውሮፕላኖች ጭምር።

ጫት ማሕበራዊ ርቀት አይጠብቅም፣ እጅዎን ወደ አፍዎ አትስደዱ አያውቅም። የሶማሊያ መንግሥት በረራ ሲያግድ ይህንንም ከግምት በማስገባት ነበር። ጫት በእጅ ስለሚለቀም ኮቪድ-19ን ለማስፋፋት ሁነኛ ነው በማለት ነበር ያገደው።

ሚራ ግን መላ አላጣም። ሶማሊያውያን በድብቅ ቢሆን እየቃሙ ነው። ጫት ከኢትዮጵያ በመኪና ተጭኖ ይመጣል። ከኬንያ ደግሞ በጀልባ እየተንሳፈፈ ሞጋዲሹ ከች ይላል።

ኬንያ እምብርት ላይ የምትገኘው ሜሩ የተሰኘችው ግዛት የጫት አውድማ ናት። ጫት አምራችና አከፋፋዮች በቀን እስከ 250 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ጫት ወደ ሞጋዲሹ ይልካሉ። በብርኛ ሲሰላ ወደ 8.5 ሚሊዮን ይጠጋል።

የአፍሪካ ቀንድ አገራት ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ገደማ ጫት አምራች ገበሬዎች እንዳሉ ይገመታል። የሶማሊያ መንግሥት እግድ ምጣኔ ኃብታዊ ቀውሱ የሚታየው ገበሬዎች ላይ ነው።

የሞጋዲሹ ጫት ነጋዴዎች ድብርት ተጫጭኗቸዋል። እነሱም ያዛጋሉ ደንበኞቻቸውም ቤት ሆነው ይተክዛሉ። አንዳንዶች ደግሞ እገዳው ኃብት ሆኗቸዋል። ጫት በድብቅ የማስገባት አቅሙ ያላቸው በፊት በኪሎ 20 ዶላር የነበረው እስከ 120 ድረስ እየቸበቸቡ ነው።

'ጫት ያልቃመ ሰው ከውሃ እንደወጣ ዓሳ ነው' ይላል በርትቶ ቃሚው ሞሐመድ አሊ። ሞጋዲሹ እንዲህ ጫት አልባ ትሆናለች ብዬ ግምቼ አላውቅም የሚለው ሞሐመድ በድብቅ የሚገባ ጫት ገዝቶ ለመቃም አቅሙ አልፈቀደም።

ሃሰን አብዲዋሊም የጫት ዋጋ እንዲህ ጣራ ነክቶ እንዴት ነው የምቅመው? ይላል። ብዙዎች ጫት ሲወደድባቸው ወደ ሌሎች አደንዛዥ ዕፆች ፊታቸውን እያዞሩ እንደሆነ ሃሰን ይናገራል።

ሶማሊያ ውስጥ ጫት የከተሜው ሱስ ብቻ አይደለም። ፖሊስና ወታደር ጫት ሳይቅሙ አይውሉም ይባላል። አሁን አሁን ጫት ዋጋው ሲወደድ ደግሞ የፀጥታ ሰዎች ስልክና ገንዘብ እየዘረፉ በመሸጥ ጫት እየገዙ ነው የሚሉ ዘገባዎች መሰማት ጀምረዋል።

ሶማሊያ ብቻ ሳትሆን ሶማሊላንድም ጫትን አግዳለች። የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት የጫት እግዱን ከቅዱሱ የረመዳን ወር ፆም በኋላ እናነሳው ይሆናል ይላሉ።

የሶማሊላንድ ጫት ምንጭ ኢትዮጵያ ናት። ምሳ ሰዓት ላይ የመኪና ጥሩንባ ከዚም ከዚያም ቢሰሙ እንዳይደነቁ። ጫት ጭነው ከኢትዮጵያ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ናቸውና።

ጫት ሻጮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

አሁን ግን መኪናዎቹ አይደለም ጥሩንባ የሞተር ድምፃቸውንም ቢችሉ አጥፍተው ነው የሚመጡት። ጫት ጭኖ የተገኘ መኪና ወዮለት። ጫቱ የእሳት ሰለባ ይሆናል።

ጫት ለአእምሮ ጤና በጎ አይደለም የሚል ፀረ-ጫት እንቅስቃሴ አራማጆች እገዳው ቢቀጥል ይላሉ። አዋሌ የፀረ-ጫት እንቅስቃሴ አራማጅ ነው። ጫት አካላዊ ጤናን ይጎዳል፣ ጥርስ ይበላል፣ ለአፍ ካንሰርም ያጋልጣል፣ አእምሯዊ ጉዳቱን ያው ታውቁታላችሁ ይላል።

የጤና ባለሙያዎችም ቢሆን ጫት አዘውትሮ መቃም ለከፋ አደጋ ያጋልጣል ይላሉ። ዩናይትድ ኪንግደም ጫትን ያገደችው በፈረንጆቹ 2014 ነበር። ደረጃ ሐ አደንዛዥ ዕፅ የሚል ታርጋም ተሰጥቶታል።

አዋሌ፤ ሶማሊላንድም ሆነች ሶማሊያ፤ እንዲሁም ኬንያና ኢትዮጵያ ጫትን እስከ ወዲያኛው ቢያግዱት ይመርጣል።

ነገር ግን ጫት እንዲሁ በቀላሉ ከገበያ ይጠፋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ሳይሆን አይቀርም። ጫት በሦስቱም አገራት ከምጣኔ ኃብታዊ መሠረታውያን አንዱ ነው። አልፎም የምጣኔ ኃብት ፖሊሲ አርቃቂዎች ፖሊሲ የሚቀርፁት ጫት እየቃሙ ነው ተብለው ይታማሉ።

ኮሮና
Banner