አሜሪካ ቻይናን 'የኮሮናቫይረስ ምርምሬን መዘበረች' ስትል ወነጀለች

ምርምር ሲደረግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከቻይና ጋር ግንኙነት ያላቸው የኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች (ሀከርስ)፤ አሜሪካ ውስጥ በኮቪድ-19 ላይ ምርምር እያደረጉ ያሉ ተቋሞች ላይ እንዳነጣጠሩ የአሜሪካ ባላሥልጣኖች ተናገሩ።

የአገሪቱ መርማሪ ድርጅት ኤፍቢአይ፤ በክትባት፣ በሕክምና እና በቫይረሱ ምርመራ ላይ እየተሠሩ ያሉ ጥናቶችን የመመዝበር ሙከራ ተደርጓል ብሏል።

አሜሪካ ቻይና እየሰለለችኝ ነው ብላ ስትወነጅል የመጀመሪያዋ አይደለም። ቻይና ግን ክሱን አጣጥላለች።

ወረርሽኙ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ውጥረት አክርሮታል። አንዳቸው ሌላቸውን 'የበሽታውን ሥርጭት መቆጣጠር አልቻልሽም' ሲሉም ይካሰሳሉ።

በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ4.3 ሚሊዮን አልፏል። በአሜሪካ 83,000፣ በቻይና ደግሞ 4,600 ሰዎች መሞታቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ያሳያል።

ኤፍቢአይ ከአገሪቱ የመረጃ ደኅንነት ተቋም ጋር በጥምረት በሰጡት መግለጫ፤ የጤና ተቋሞች እንዲሁም የጥናት ማዕከሎች ዋነኛ ኢላማ ናቸው ብለዋል።

"መረጃ መዝባሪዎቹ ጠቃሚ ሰነዶችና የሕብረተሰብ ጤና መረጃ ለመሰብሰብ ሞክረዋል" ተብሏል በመግለጫው።

የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ዛሆ ሊያነ "በኮቪድ-19 ሕክምና እና ክትባቱን ለማግኘት በሚደረግ ምርምርም ከዓለም ቀዳሚ ነን። ምንም ማስረጃ ሳይኖር የቻይናን ስም ማጥፋት ሥነ ምግባር አልባነት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ በሰጡት መግለጫ ላይ "በቻይና ደስተኛ አይደለሁም። ከመነሻው መግታት ትችል ነበር፤ ከመነሻው ማቆም ነበረባት። አሁን ደግሞ መረጃችንን መመዝበር ጀመሩ? በቅርበት እየተከታተልናቸው ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

አሜሪካና ዩናይትድ ኪንግደም ሌሎች አገራት ጥናቶቻችን ላይ አነጣጥረዋል ሲሉ በጋራ ማስጠንቀቂያ የሰጡት ግንቦት መግቢያ ላይ ነበር።

ማስጠንቀቂያው ለየትኞቹ አገራት እንደነበረ በይፋ ባይገለጽም፤ ቻይና፣ ሩስያና ኢራን ተጠያቂ ከተደረጉት መካከል እንደሚገኙበት ውስጥ አዋቂ ምንጮች ጠቁመዋል።

አሁን ደግሞ አሜሪካ ቻይና አሜሪካን ነጥላ እየወቀሰች ነው። ዩናይትድ ኪንግደም ግን እስካሁን ያለችው ነገር የለም።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከመነሳቱ በፊትም አሜሪካ ቻይናን በስለላ ትወነጅላለች።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2009 ላይ አሜሪካ፤ ቻይና 'ማርቲን ኤፍ-35' ስለተባለው ተዋጊ ጀት መረጃ እንደመዘበረች ተናግራ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ቻይና 'ሸንያንግ ጂ-31' የተባለና ከአሜሪካው ተዋጊ ጀት ጋር የሚመሳሰል ጀት መሥራቷን ይፋ አድርጋለች።

የአሜሪካ ደኅንነት ተቋም ኃላፊ እንደሚሉት፤ ቻይና ከአሜሪካ የዘረፈችው አዕምሯዊ ንብረት በዓመት 400 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ያወጣል።

ኮሮና
Banner