የመቅመስና የማሽተት ስሜት ሳይኖር ሼፍ መሆን ይቻላል?

የፎቶው ባለመብት, Mel Yu Vanti
በዓለም ላይ በሙዚቃ ታሪከ አዋቂዎች ዘንድ ከሚዘከሩትና ሊቅ ከሚባሉት መካከል አንዱ ቤትሆቨን ነው።
ቤትሆቨን በሙዚቃው መጠበቡ ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን የሚያስደንቀው ከ28 ዓመቱ በኋላ የመስማት ችገር አጋጥሞት 44 ዓመቱም ላይ ሙሉ በሙሉ መስማት አይችልም ነበር።
መስማት ሳይችል እንዴት ሙዚቃን አቀናበረ? የሚለው ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል። ብዙዎችም በህይወት የሚያጋጥም ተቃርኖ ይሉታል።
በካናዳ ውስጥ ታዋቂ የምግብ አብሳይ (ሼፍ) የሆነችው ጆሽና ማሃራጅም ይሄው ተቃርኖ ሊባል የሚችል ጉዳይ ገጥሟታል። ለአምስት ዓመታትም ያህል የማሸተትም ሆነ የመቅመስ ስሜቷን እንዳጣችም ከወራት በፊት ይፋ አድርጋለች።
ያጣችውንም የስሜት ህዋሷን ለመመለስ እንዲሁ እየደከመች ነው። በመጀመሪያ ያጣችው የማሽተት ስሜቷን ሲሆን እንዲሁ በአንድ ሌሊት አይደለም። ቀስ በቀስ ነበር።
በመጀመሪያው ላይ ምግብ ማሳረር ጀመረች፤ የኮክ ኬክ እየጋገረች፣ ቀምበር ማለት ቢኖርበትም ማሽተት ባለመቻሏ አሮ ወጣ።
"አንዳንዴ ያረረውን ቆርሶ ማቅረብ ይቻል ይሆናል። በዚህ ወቅት ግን ሙሉ በሙሉ በማረሩ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ተጣለ" ትላለች።
በሌላ አጋጣሚም እንዲሁ ከጓደኞቿ ጋር ታዋቂ የሥጋ ጥብስ የሚሸጥበት ሬስቶራንት እያለፉ፤ ጓደኞቿ በሥጋው ጥብስ መዓዛ ሲደመሙ እሷ ግን ምንም ማሽተት አልቻለችም።
"መጀመሪያ አልገባኝም ነበር ችግሩ፤ በኋላም ሁኔታዎችን ስከታተል፤ አፍንጫዬ ማሽተት አይችልም የሚለው ተገለፀልኝ" ትላለች።
"እውነቱን ለመናገር በወቅቱ መንፈሴ በሙሉ ነው የተረበሸው። ማሽተት ሳልችል እንዴት ሼፍ እሆናለሁ የሚለውም ያስጨንቀኝ ጀመር። ሥራዬን ላቁመው የሚለውም ሃሳብ ይመላለስብኝ ነበር" ትላለች።
ሆኖም የሆዷን በሆዷ ለማድረግ ወሰነች "ምስጢርሽን ትደብቂያለሽ፤ ማንም ቢሆን መስማት የለበትም" በማለትም ከእራሷ ጋር ንግግር አድርጋ ወሰነች።
ቶሮንቶ ተወልዳ ያደገችው ጆሽና፤ የሥርዓተ ምግብ መብት አቀንቃኝ፣ ደራሲ ስትሆን በዓለም ላይ ካሉ ታዋቂ የሕዝብ ተቋማት፣ ዩኒቨርስቲዎችና ሆስፒታሎች ምግብ በምን መንገድ ማብሰል እንዳለባቸውና ለአቀራረቡም የተለየ እሳቤ በማምጣት ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ችላለች ይሏታል።
በአሁኑ ወቅት ግን 'አኖሶሚያ' በሚባል በሸታ ተጠቅታለች፤ በሸታው ሙሉ በሙሉ የማሽተት የስሜት ህዋስን የሚያጠፋ ነው።
በዓመታት ውስጥ ምግብ መድረስ አለመድረሱን በሽታ መለየት ትችል የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ወደ ሰዓት መሙላትና የቅመም መጠናቸው ከፍተኛ ወደሚባሉ ምግቦችም ተሸጋገረች።

የፎቶው ባለመብት, Courtesy Joshna Maharaj
ጠንካራና ሸታ ያላቸውን ቅመሞች መጨመር፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ዝንጅብል እንዲሁም በቅመም ያበደውን የህንዱን ከሪ ማብሰል ጀመረች።
የማሽተትና የመቅመስ ስሜት ጠንካራ ግንኙነት መኖሩን ተከትሎ የመቅመስ ስሜቷንም ያጣችው ወዲያው ነው።
አኖሶሚያ የሚባለው ህመም በተለያዩ ምክንያቶች ይመጣል፤ በቀላሉ በቫይረስ ከመጠቃት ጀምሮ እስከ ከፍተኛው የአዕምሮ ጉዳት አኖሶሚያን ያስከትላል።
በቅርቡም ተመራማሪዎች የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ውስጥ ብለው ከጠቀሷቸው ውስጥ የመቅመስና የማሽተት ስሜትን ማጣት ይገኙበታል።
ጆሽና ማሃራጅም ለዓመታት ያህል በሳይነስ አለርጂ ትሰቃይ ነበር፤ በተደጋጋሚም ከአንገቷ በላይ ባለው የመተንፈሻ አካሏ ችግርም መፍትሄ ልታገኝለት አልቻለችም ነበር። አፍንጫዋም ስለሚታፈን መተንፈስም ከባድ ነበር።
"ያልሞከርኩት አይነት ህክምና የለም። የቻይና የአገር በቀል መድኃኒት፣ ምግብ መቀየር፣ አኩፓንክቸር እንዲሁም በተደጋጋሚ በአፍንጫ የሚወሰድ መድኃኒት ወስጃለሁ" ትላለች።
በባለፈው ዓመትም ይህንኑ ለማስተካከል ቀዶ ጥገና አድርጋ በወራት ውስጥም የማሽተት ስሜቷ ትንሽ ተመለሰ።
የህንዷን ባንጋሎር ግዛት እየጎበኘች ባለችበት ወቅት ድንገት የማንጎ ሽታ ሸተታት፤ ራሷን ተጠራጠረች። ሆቴሏም ስትመለስ በእንግዳ መቀበያው አካባቢ የአበባ ሽታ ሸተታት። ሆኖም በሚያሳዝን ሁኔታ ማሽተትም ሆነ መቅመስ የቻለችው ለሁለት ሳምንታት ብቻ ነበር።
በተለይም ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ ክሮሺያ በሄደችበት ወቅት ሁኔታው በጣም ከብዷት ነበር። ቤተሰቧ ጋር የተለያዩ ሬስቶራንቶች ሄደው የምግቡን ጣዕም ሲያመሰግኑ፣ በምግብ ሽታ ሲደመሙ ለእሷ ግን ሁሉ ነገር ባዶ ነበር።
ያልናፈቀችው አይነት ሽታ የለም። ነጭ ሸንኩርት፣ ዝንጅብል ቁሌት፣ የአራስ ልጅ ሽታ...
"ጓደኛዬ ከወራት በፊት ስትወልድ ፊቴን አስጠግቼ ጨቅላውን ለማሽተት ሞከርኩ። ምንም ነገር አልሸተተኝም። በጣም ነው ልቤ የተሰበረው፤ ሐዘኔ ጥልቅ ነው" ትላለች።
ይባስ ብሎ ማሸተት ከተለያዩ የሰው ልጅ ስሜቶች ጋር ግንኙነት እንዳለው አንድ ጓደኛዋ ነግሯት ጠለቅ ብላም የተለያዩ ምርምሮችን ማንበብ ጀመረች። የማሽተት ስሜት ማጣት ለድብርት፣ ጭንቀት እንደሚያጋልጥም መረጃዎችን አገኘች።
ይህንኑም ተከትሎ ስለህመሟ ለሌሎች ሰዎችም መናገር እንዳለባትና መፍትሔም መፈለግ እንዳለባት ተረዳች።
በኢንስታግራም ገጿም ላይ ስለ ችግሯ ፃፈች። በመቀጠልም እንደ አዲስ የማሽተት ስልጠናንም መውሰድ ጀመረች፤ አዕምሮዋንና አፍንጫዋን የሚያገናኘውንም መስመር ለመጠገንም ህክምና እንደገና ጀመረች።
በለንደን ተቀማጭነቱን ያደረገና የሽታና የመቅመስ ስሜታቸውን ላጡ እንደገና የሚመልሱበትን፤ እንዲሁም ግንዛቤ በማዳበር ላይ የሚሰራ 'አብሰንት' የሚባል ድርጅትም አገኘች።
በዓለም ላይ 5 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የማሽተት ስሜት በማጣት እንደሚሰቃይ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
"የተለያየ ምግብ መብላትና መጠጥ መጠጣት ለሚወዱ፤ ማብሰልን ለሚናፍቁ ሰዎች የማሽተትና የመቅመስ ስሜትን ማጣት ማለት ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ መግባት ነው" ትላለች።
ከዓመታት በፊት ማሽተትን ብዙም ልብ ብላ አስባው አታውቅም ነበር። ነገር ግን ስታጣው የቤቷ ሽታ ይናፍቃታል፣ የታጠበ ልብስ. . . ምን የማይናፍቃት ነገር አለ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Creative Stock
የተለያዩ ምርምሮች እንደሚጠቁሙት ምንም እንኳን የማሽተት ስልጠና ሙሉ በሙሉ ማሽተትን ባይመልስም የአእምሮ ነርቮችን በማነቃቃት እንዲያገግሙ ለማድረግ ይቻላል።
ለአፍንጫ የቴራፒ ህክምና እንደመውሰድ ማለት ነው።
ስልጠናውም ሽታቸው ጠንካራ የሆኑ ዘይቶች፣ በተለይም የፍራፍሬ ዘይት ያላቸው በመጠቀም የሚሰጠጥ ነው።
አራት አይነት ዘይቶችን፤ እያንዳንዱን ለሃያ ሰከንዶች በቀን ውስጥ ሁለት ጊዜ ማሽተት። በተቻለ መጠን የማሽተቱን ስሜትን መመለስ ብቻ ሳይሆን አእምሮንም ከዚህ ቀደም ያንን ሸታ እንዲያስታውስ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል።
ጆሽና ማሃራጅም የባህር ዛፍ፣ ሮዝ አበባ፣ ሎሚና ቅርንፉድ ዘይቶችን መረጠች።
ቁጭ ብላም መጀመሪያ የባህር ዛፉን ዘይት እያሸተተች በጭንቅላቷ ስቲም የሚወሰድበት ክፍልን ታስባለች፤ ሎሚን ስታስብ ደግሞ ሎሚ ሲጨመቅ የነበረውን ሽታ አእምሮዋ እንዲያስታውሰው ትጥራለች።

የሮዝ አበባንም ከዓመታት በፊት ያሸተተችውን ጣዕሙ ለስለስ ያለውን ለማስታወስ በጭንቅላቷ እያሰላሰለች ትሞክራለች።
ለጆሽና ማሃራጅ ሸታም ሆነ መቅመስ ከትዝታዋ ጋር በጣም የተቆራኘ ነው።
የቅርንፉድ ሽታ ከልጅነቷ የገና ወቅት እንዲሁም ለክረምት ምግብ ሲቁላላ የነበረው የቅመሙን ሽታ፣ ትንሽ የሚያቃጥል ጣዕምን በጭንቅላቷ ለማስታወስ ከፍተኛ ትግል ታደርጋለች።
ለአንድ ወርም ያህል ምንም ነገር ማሸተት አልቻለችም። በቅርቡ ግን የባህር ዛፍም ሳይሆን የቅርንፉድ የሆነ ሽታ ብልጭ አለላት።
ሽታው ምን እንደሆነ ለመለየት ብትታገልም ማወቅ አልቻለችም። ቀስ በቀስም የማሸተት ስሜቷ ቢመለስም በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ጠፋ።
'አብሰንት' እንደሚለው የሽታን ስሜት ጭላንጭሉን ለማምጣት ቢያንስ አንድ ወር ይፈጃል።
ሆኖም ለጆሽና የማሽተት ስሜት ባይኖራትም የቅምሻ ጣዕሟ በትንሹም ቢሆን ተመልሷል። በተለይም ታበስል የነበረው በትዝታ ከመሆኑ አንፃር አሁንም ትንሽም ቢሆን ማጣጣም መቻሏ አስዳሳች ሆኖላታል።












