ኢራን የሕዝብ ቁጥሯን ለማሳደግ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ማቅረብ አቆመች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ኢራን የሕዝብ ቁጥሯን ከፍ ለማድረግ በሚል በመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ ይቀርብ የነበረው የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት አቅርቦትን ውስን አደረገች።
በዚህም በመንግሥት በሚተዳደሩ ሆስፒታሎች ውስጥ እርግዝና በጤናቸው ላይ እክል ለሚያስከትልባቸው ሴቶች ብቻ የእርግዝና መከላከያዎች የሚሰጥ ሲሆን፤ በወንዶች ላይ ይደረግ የነበረው ቫሴክቶሚ የተባለው ቀዶ ህክምና እንዳይካሄድ ተደርጓል።
ነገር ግን የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶቹ በግል ሆስፒታሎች ውስጥ እንደሚሰጡ ታውቋል።
የኢራን መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ የሚመዘገበው ዝቅተኛ የወሊድ መጠንና እየጨመረ የመጣው እድሜያቸው እየገፋ የሚሄድ ሰዎች ቁጥር አሳስቦታል።
የኢራን አመታዊ የሕዝብ ቁጥር እድገት በአንድ በመቶ እየቀነሰ ሲሆን፤ በቶሎ ርምጃ ካልተወሰደ አገሪቱ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ውስጥ በርካታ በእድሜ የገፉ ዜጎች ካላቸው አገራት ተርታ ውስጥ እንደምትገባ የአገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ኢራን የሕዝብ ብዛቷ 1.4 በመቶ ማስመዝገቧ ተገልጾ ነበር። ይህ አሃዝ በጎረቤቷ ኢራቅ ውስጥ 2.3 በመቶ ሲሆን ባላንጣዋ ሳኡዲ አረቢያ ደግሞ 1.8 በመቶ የሕዝብ ቁጥር እድገት ማስመዝገባቸውን የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል።
የአገሪቱ መንግሥት የዜና ተቋም የሆነው ኢርና እንደዘገበው ጋብቻ እና በጋብቻ ውስጥ የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ቀንሷል፤ ለዚህም ምክንያቱ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንደሆነ አመልክቷል።
ግንቦት ወር ላይ የጤና ጥበቃ ምክትል ሚኒስትሩ ሰይድ ሐሚድ ባራካቲ እንደተናገሩት በኢራን ውስጥ ያለው የጋብቻ መጠን በአስር ዓመት ውስጥ በ40 በመቶ ቀንሷል።
"በዚሁ የምንቀጥል ከሆነ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ውስጥ በዕድሜ የገፉ በርካታ ሕዝብ ካላቸው አገራት አንዱ እንሆናለን" ብለዋል ምክትል ሚኒስትሩ።
እንደ አውሮፓዊያኑ በ1979 የተካሄደው እስላማዊ አብዮትን ተከትሎ የሕዝብ ቁጥሯ በከፍተኛ መጠን ጨምሮ ነበር። ነገር ግን ከዚያ በኋላ ውጤታማ የሕዝብ ብዛት መቆጣጠሪያ ፖሊሲ በመከተሏ አሁን የታየው ውጤት መመዝገቡ ተገልጿል።
የአገሪቱ የበላይ መሪ የሆኑት አያቶላህ አሊ ኻሚኒ ሕዝቡ በርካታ ልጆች እንዲኖሩት ሲያበረታቱ ቆይተዋል። እንደ እሳቸው ፍላጎት ኢራን አሁን ካላት 80 ሚሊዮን ሕዝብ ወደ ግማሽ የሚጠጋ ጭማሪ አድርጋ ቁጥሩ ወደ 150 ሚሊዮን ከፍ እንዲል ይሻሉ።












