የ68 ዓመቷ ናይጄሪያዊት አዛውንት መንታ ልጆች ተገላገሉ

የፎቶው ባለመብት, LUTH
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዜና የመገናኛ ብዙሃንን ባጨናነቀበት በአሁኑ ወቅት ከወደ ናይጄሪያ የተሰማው ዜና ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።
ክስተቱ አዲስ ባይሆንም ብዙም የተለመደና የሚጠበቅ አይደለም፤ አንዲት ወደ 70 ዓመት የተቃረቡ አዛውንት ለወራት አርግዘው ጨቅላ ህጻናትን ታቅፈዋል።
በዚህም የናይጄሪያው የሌጎስ ግዛት ዩኒቨርሲቲ መማሪያ ሆስፒታል አንዲት የ68 ዓመት እናትን መንታ ልጆች በሰላም እንዲገላገሉ ማድረጉን አስታቋል።
የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ የህክምና አማካሪዎች ቡድን ሊቀ መንበር የሆኑት ፕሮፌሰር ዋሲኡ አዲዬሞ እንዳሉት የ68 ዓመቷ እናት በተሳካ ሁኔታ መንታ ህፋናትን የወለዱት ትናንት እሁድ ነው።
አዛውንቷ እናት መንታ ልጆቻቸውን የወለዱት በ37ኛ የእርግዝና ሳምንታቸው በቀዶ ህክምና መሆኑንም ዩኒቨርስቲው ጨምሮ ገልጿል።
ከተሳካው የቀዶ ህክምና ማዋለድ በኋላ አራሷ የ68 ዓመቷ እናት እና ልጆች በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም ተነግሯል።
መውለድ አይቻልም በሚባልበት የዕድሜ ክልል የሚገኙት እናት ቀደም ሲል ምንም ልጅ ያልነበራቸው ሲሆን ትናንት የተገላገሏቸው መንታ ህጻንት የመጀመሪያ ልጆቻቸው ናቸው ተብሏል።
ይህንንም ፕሮፌሰር ዋሲኡ አዲዬሞ የእኚህ እናት እርግዝና የመጀመሪያቸው መሆኑን ለናይጄሪያ የዜና የዜና አገልግሎት ተናግረዋል።












