"የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ልጆች በመሆናችን ብቻ መታሰርና መንገላታችን ያሳዝናል" ቦንቱ በቀለ።

ቦንቱ በቀለ

የፎቶው ባለመብት, Addis Standard

የሃጫሉ ሁንዴሳ መገደልን ተከትሎ በተከሰተው አለመረጋጋት ለእስር ከበቁት ሰዎች መካከል ፖለቲከኞቹ አቶ በቀለ ገርባ፣ ጃዋር መሃመድ ይገኙበታል።

ከነሱም በተጨማሪ የአቶ በቀለ ገርባ ሁለት ልጆች ቦንቱና ሳሙኤል እንዲሁም የእህታቸው የልጅ ልጅም ኪያ በላቸው ሰኔ 23/2012 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።

ቦንቱ በቀለ ከሁለት ሳምንታት እስር በኋላ ሐሙስ ሐምሌ 9/2012 ምሳ ሰኣት አካባቢ ተፈትታለቸ።

ለአስራ አምስት ቀናትም ቦንቱ በፌደራል ወንጀል ምርመራ እስር ቤት ውስጥ የቆየች ሲሆን ሳሙኤልና ኪያ ደግሞ ጉለሌ አካባቢ በሚገኝ ትምህርት ቤት ውስጥም ታስረው እንደነበር ትናገራለች።

ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው በፊት ማንም አካል በቁጥጥር ስር የዋሉበትን ምክንያት እንዳልነገራቸው፣ ፍርድ ቤቱ ሲቀርቡ ግን ተጠርጥረው የታሰሩበትን ምክንያት ፖሊሱ ክሱን ሲያነብ መስማቷን ለቢቢሲ ገልጻለች።

አባቷ አቶ በቀለ ገርባና ቤተሰቦቿን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር የዋሉት በኦሮሞ ባህል ማዕከል ሲሆን በቀጥታ ወደ ፌደራል ወንጀል ምርመራ መወሰዳቸውን ትናገራለች።

"ወደ ፌደራል ወንጀል ምርመራ ተወሰድን፤ ኮሪደር መሃል ነው ያሳደሩን፤ ወለል ላይ ነው ተኝተን ያደርነው" በማለት የመጀመሪያ ምሽታቸውን እንዴት እንዳሳለፉ ታስረዳለች።

በማግስቱ ጠዋት ወደ ኦሮሞ ባህል ማዕከል ቢወሰዱም ሳያስገቧቸው መመለሳቸውን የምትናገረዋ ቦንቱ፣ በእስር የቆየችባቸውን 17 ቀናት በዚያው በፌደራል ወንጀል ምርመራ እስር ቤት ውስጥ ማሳለፏን ገልፃለች።

ፍርድ ቤት የተነበበው ክስ "የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊስን ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን በመግደል" እንደሚልም ቦንቱ ትናገራለች።

በፖሊስ መግደል ተጠርጥራ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ስትፈታ የተሰጣት ምክንያት ምን እንደሆ ቢቢሲ የጠየቋት ሲሆን ከማረፊያ ቤት ተጠርታ ታጅባ ወደ ቢሮ መሄዷንና የዋስትና ቅጽ የሚል ወረቀት ላይ ከፈረመች በኋላ እቃዎቿን ይዛ እንድትወጣ ብቻ እንደተነገራት ተናግራለች።

ወንድሟ ሳሙኤልና ኪያም የተገናኙት ከመሸ በኋላ ተለቅቀው ቤት ሲመጡ መሆኑንና ዳግመኛ ቃላቸውን መስጠታቸው፣ ከዚያ በኋላም ፈርመው መለቀቃቸውን እንደነገሯት ገልፃለች።

የማረሚያ ቤት ቆይታ

ቦንቱ ለአስራ ሰባት ቀን የቆየችበት ማረሚያ ቤትን ስትገልፅ፣ የመጀመሪያዎቹ አራት ቀናት መስኮት ያለበት ክፍል ውስጥ መታሰሯንና መስኮቱ እንደሚከፈትና ብርሃን ያስገባም ነበር ብላለች።

መስኮቱ ወደ ወንዶች ክፍል ስለሚያሳይ አባቷን አቶ በቀለ ገርባንና ጃዋር መሐመድን ማግኘቷን እና ማውራትም ችላ ነበር።

ከአራተኛው ቀን በኋላ ግን አባቷንና ጃዋርን በመስኮት በኩል ማግኘቷን ፖሊሶች በማወቃቸው ወደ ሌላ ክፍል ተዛወረች።

የተዛወረችበት ክፍል እርሷ ከመምጣቷ በፊት የነበሩበት እስረኞች ሲናገሩ ሰማሁት በማለት፣ "መስኮቱ ስለማይከፈት በሩ አይቆለፍም ነበር" ትላለች።

እርሷ ከገባች በኋላ በሩ መዘጋት መጀመሩን፣ መታጠብያ ክፍል ለመሄድም ሆነ ለመታጠብ ማንኳኳትና ፈቃድ መጠየቅ ያስፈልግ እንደነበር የምትገልፀው ቦንቱ አንዳንድ ጊዜ ፈቃደኛ የማይሆኑበት ወቅት እንደነበር ታስታውሳለች።

በእስር ቤት ክፍሉ ውስጥ የደህንነት ካሜራ የተገጠመ ሲሆን ከክፍሉ ጀርባም ካሜራውን የሚቆጣጠሩ ሰዎች ቢሮ እንዳለም ተረድታለች።

አመሻሽ 12 ሰዓት የታሰሩበት ክፍል ስለሚቆለፍ እና ከዚያ በኋላ ወደ መታጠብያ ክፍል ለመሄድ ስለማይፈቀድም ሌሊት ወደ ንጽህና ቤት ለመሄድ የሚፈልግ ሰው እንደሚቸገር፣ የታሰሩበት ክፍል ውስጥም ለመጠቀም ካሜራ በመኖሩ ምክንያት የማይቻል ነበር።

ክፍሉ በጣም እንደሚቀዘቅዝ አክላለች።

መጀመሪያ በቁጥጥር ስር ሲውሉ 26 የነበሩ ሲሆን ከመካከላቸው አንዱ በኮሮናቫይረስ መያዙ ስለተጠርጠረ ወደ ሌላ ስፍራ ለህክምና ክትትል መወሰዱን ገልፃለች።

በእስር ቤት ቆይታዋ ወቅት ምንም ዓይነት አካላዊ ጥቃት ባይደርስባትም ነገር ግን ከሌሎች ሴት እስረኞች በተለየ በትኩረት ይከታተሏት እንደነበር ትናገራለች።

ወንድሟ እና የአክስቷ ልጅም ላይ እንዲሁ ምንም ዓይነት አካላዊ ጉዳት ያልደረሰባቸው ሲሆን ወንድሟ በእስር ቤት ቆይታው ያስፈልገው የነበረውን የህክምና ክትትል ያገኝ እንደነበር እንደነገራትም ጨምራ አስረድታለች።

አባታቸውን ሰላማዊ ትግል የሚያደርግ መሆኑን በመግለጽ ቤተሰቡ የእርሳቸውን አላማም ቢደግፍም በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ተሳትፎ እንደሌላትም ለቢቢሲ ተናግራለች።

"አባቴ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር በመሆኑ እና እኛ በዚህ ዓይነት መልኩ በመንገላታታችን በጣም ነው የምናዝነው" ስትል የአቶ በቀለ ገርባ ልጅ በመሆኗ እና አብራቸው በመገኘቷ ብቻ እስርና እንግልት እንደደረሰባትም ገልፃለች።

ከአሁን በኋላ የቤተሰቡ ሙሉ ትኩረት የአቶ በቀለ ገርባን ሁኔታ መከታተል ነውም ትላለች።

"እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም ሌላ ሥራ ላይ ነው የተሰማራሁት" የምትለው ቦንቱ እንደ ልጅ አባቷ የሚያስፈልጋቸውን እንደምታደርግ፣ ፍርድ ቤት መገኘት፣ ስንቅ ማድረስ፣ ከጠበቆች ጋር መነጋገር ቀጣዩ ሥራዋ እንደሚሆን ገልጻለች።

"ነገር ግን እንደ አባቴ በእኩልነት፣ በዲሞክራሲ ሃሳብን በነጻነት መግለጽን የማምን ሰው ነኝ። ሁሌም ኢ-ፍትሃዊነትን፣ አድሏዊነትን የምቃወም ሰው ነኝ" በማለት በየትኛውም ድርጅት ውስጥ የፖለቲካ ተሳትፎ እንደሌላት ተናግራለች።