"ተደብድበሃል ወይ? ብዬ ጠይቄዋለሁ" የአቶ በቀለ ገርባ ባለቤት

አቶ በቀለ ገርባ

የፎቶው ባለመብት, CHRIS STEIN

በዛሬው ዕለት በፖሊስ አባል ግድያ ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡትን አቶ በቀለ ገርባን መድኃኒት እንዳደረሱላቸው "ድብደባ ደርሶብሃል? ወይ" ብለው እንደጠየቁዋቸው ባለቤታቸው ወይዘሮ ሃና ረጋሳ ለቢቢሲ ማምሻውን ተናግረዋል።

ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የአስከሬን ሽኝት መስተጓጎልና ከአንድ የፖሊስ አባል ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙት አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባ በሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙም አስረድተዋል።

ከሁለት ልጆቻቸው ቦንቱና ሳሙኤል እንዲሁም የእህታቸው የልጅ ልጅም ኪያ በላቸው በእስር ላይ እንደሚገኙ የገለፁት ወይዘሮ ሃና እስራቸው ያልጠበቁትና ምንም ሳይሰሙም መሽቶ መንጋቱን ተናግረዋል።

በትናንትናው ዕለት ሰኔ 24፣ 2012ዓ.ም ስድስት ሰዓት አካባቢ የእስረኞች አስተዳደር ኃላፊ ደውሎ "አቶ በቀለ መድኃኒት ይፈልጋሉ ቶሎ ብላችሁ መድኃኒት ይዛችሁ ኑ" እንደተባሉና መድኃኒቱን እንዲሁም ውሃ ይዘው ሄደዋል።

የአቶ በቀለ ገርባ የመጨረሻ ልጅ የሆነው ዳዊት፣ አባቱ የደም ግፊት ስላለባቸው በተከታታይ መውሰድ የነበረባቸው መድኃኒት አለ በማለት "መድኃኒት እንድናመጣ ተነገረን" ሲል ይገልጻል።

በትናንትናው እለትም መድኃኒት ሲያደርሱላቸው በአይን እንዳይዋቸው የሚናገረው ዳዊት ዛሬ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።

በዚያኑ ቀንም ከሰዓት በድጋሚ ተደውሎላቸው ምግብና ልብስ ይዘው እንዲያመጡ የተጠየቁ ሲሆን በርቀትም ማየታቸውንም ተናግረዋል።

በዛሬውም እለት ጠዋት ምግብ ይዘው ቢሄዱም ፍርድ ቤት ስለነበሩ ማግኘት እንዳልቻሉና በጣቢያው እየጠበቁ በነበረበት ወቅትም ቤታቸው ሊፈተሽ ስለሆነ በአስቸኳይ እንዲመጡ የሚል ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል።

አቶ በቀለ ከፖሊሶቹ ጋር እንዳሉ እንዲሁም የፍርድ ቤት ማዘዣ መያዛቸውን እንደነገሯቸው የሚያስታውሰው ዳዊት መጥተው ቤቱን እንዲከፍቱላቸው ፖሊሶቹ መጠየቃቸውን ገልጿል።

ቤትም ደርሰው ለሁለት ሰዓታት ያህል ለሚፈጅ ጊዜም ቤታቸው መፈተሹንም ወይዘሮ ሃና ይናገራሉ።

እንደ ወይዘሮ ሃና የአቶ በቀለ ሦስት ማስታወሻዎች፣ እንዲሁም የስብሰባ ጥሪዎችና ወረቀቶች ተወስደዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሽጉጥም መወሰዱንም ጭምር አስረድተዋል።

በወቅቱም የአቶ በቀለ የቀኝ አይናቸው ቀልቶ እንዲሁም አበጥ ብሎ እንዳዩት የሚናገሩት ወይዘሮ ሃና ሁኔታውን ጠይቀዋቸዋል። ''ደብድበውሃል ወይ?'' ብለው እንደጠየቁዋቸው ከአመሻሹ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል።

"ለነገሩ አይኑን ከበፊትም ያመው ነበር፤ ምን ሆኖ አበጠ ስለው፤ አላውቅም የተኛንበት ፍራሽም እንዲሁም ለብሰን ያደርነው ሊሆን ይችላል፤ ሲያሳክከኝ እንደ አለርጂ ነው መሰለኝ ሳከው አበጠ" ብለው እንደመለሱላቸውና "ደብድበውሃል ወይ ለሚለው ጥያቄም ማንም አልነካኝም" ብለዋቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በሰዓቱ ስለ ክሱም ለመነጋገር እድል ያገኙ ሲሆን ፍርድ ቤት ብቻቸውን እንደቀረቡና በግድያ ወንጀል ተጠርጥረውም እንደሆነ ለባለቤታቸው እንዲሁም ለልጃቸው ዳዊት አስረድተዋቸዋል።

ከዚህ በፊት ከነበሯቸው ጠበቆች ጋር መገናኘት ባለመቻላቸው እንዲሁም ያለ ጠበቃ በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን ለወደፊቱም ጠበቃ እንደሚያቆሙም ወይዘሮ ሃና ተናግረዋል።

በማን ግድያ እንደተጠረጠሩ እንዳልተነገራቸው መግለፃቸውን የሚናገሩት ቤተሰቦቻቸው ከዚያ በኋላ ወይዘሮ ሃና እነሱን ተከትለው ምግብ እንዳደረሱላቸው ተናግረዋል።

የሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት የተነገራቸው በሞተበት እለት ሰኔ 22፣ 2012ዓ.ም ሌሊት ተደውሎ ሲሆን በወቅቱም አቶ በቀለ መደንገጣቸውን የሚናገሩት ባለቤታቸው በማግስቱም ሦስት ሰዓት አካባቢ ልጆቻቸው ቦንቱና ሳሙኤል ጋር ሆነው እንዲሁም አብሯቸው የሚኖር የእህታቸው የልጅ ልጅ ኪያ በላቸው አራት ሆነው ከቤት ለሽኝት እንደወጡ ይናገራሉ።

ለቅሶው ሽኝቱ አካባቢ በደረሱበት ወቅትም የሃሳብ መቀየር መጣና ሃጫሉ አምቦ መቀበር የለበትም አዲስ አበባ ይቀበር ተብሎ ሕዝቡም እንዲሰናበተው በሚል አስከሬኑ ተመልሶ ኦሮሚያ ባህል ማዕከል መግባቱን ይናገራሉ።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የፀጥታ ኃይል መጥቶ የሃጫሉን አስከሬን ይዘውት እንደወጡና ወደ ትውልድ ቦታውም አምቦ እንደወሰዱት ይናገራሉ።

አቶ በቀለና አቶ ጃዋርም እንዲሁ ከእሱ ጋር የነበሩትም ከሰዓት በኋላ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ይናገራሉ። የአቶ ጃዋር ጠባቂዎችም መሳሪያ ፍቱ ተብለው ሁሉም ተሰብሰበው እንደታሰሩ ገልፀዋል።

አንደኛዋ ልጃቸው ቦንቱ እዚያው እነ አቶ በቀለ የታሰሩበት ግቢ እንደምትገኝና ወ/ሮ ሃና እንዳዩዋትና ሰላም እንዳሏትም ገልፀዋል። ሁለቱ የቤተሰብ አባላት ጉለሌ የሚባል አካባቢ እንደታሰሩም ልጃቸው ነግራቸዋለች።

"እሱ እድሜውን ያሳለፈው በእስር ነው፤ ልጆቹን ለማሳደግ እድል ያላገኘ ሰው ነው። ሰው አክባሪ፣ አፍቃሪ ነው። . . . እስሩ ከትግሉ እንዴት እናውጣው የሚል ነው" ብለዋል።