አውስትራሊያ በዓለም ፈጣኑን ኢንተርኔት አስመዘገበች

የኢንተርኔት ገመድ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, የኢንተርኔት ገመድ

የአውስትራሊያ አጥኚዎች በዓለም ፈጣኑን በይነ መረብ [ኢንተርኔት] ማስመዝገባቸውን አሳወቁ።

በስዊምበርንና አርኤምአይቲ ዩኒቨርሰቲ ያሉ ተመራመሪዎች ያስመዘገቡት የኢንተርኔት ፍጥነት በሰከንድ 44.2 ቴራባይት ነው። ይህም ማለት ተጠቃሚዎች ከአንድ ሰከንድ ባነሰ ጊዜ 1 ሺህ ሃይ ዴፊኒሽን [ከፍተኛ የስዕል ጥራት ያላቸው] ፊልሞችን ማውረድ ይችላሉ።

የዩናይትድ ኪንግደም የቴሌኮሚኒኬሽን ኩባንያ የሆነው ኦፍኮም እንደሚለው ከሆነ በአሁኑ ወቅት የዩናይትድ ኪንግደም አማካዩ የኢንተርኔት ፍጥነት በሰከንድ 64 ሜጋባይት ነው።

አውስትራሊያ፤ በዓለማችን ካሉ ሃገራት መካከለኛ ፍጥነት ያለው ኢንተርኔት ያላት ሃገራት ናት። የኢንተርኔት ፍጥነት ቀርፋፋ መሆን ደንበኞችን ሲያማርር መስማትም የተለመደ ነው።

አጥኚዎቹ አዲሱን ፍጥነት አስመዘገብን ያሉት ማይክሮ ኮምብ የተሰኘ አንድ ቁስን ተጠቅመው ነው።

ይህ የኢንተርኔት ፍጥነት በዓለም የመጀመሪያው ሲሆን በፋይበር ኦፕቲክ ኢንተርኔት ታሪክም እጅግ ፈጣኑ ተብሎለታል።

አጥኚዎቹ የተጠቀሙት ቁስ የአውስትራሊያ ብሔራዊ ብሮድባንድ ኔትወርክ የሚጠቀመው ነው። ነገር ግን አጥኚዎቹ ቁሱ የበለጠ አንዲያገለግል አሳድገውታል።

አጥኚዎቹ ግኝታቸው ወደፊት የኢንተርኔት ፍጥነት ምን ያክል ሊረቅ እንደሚችል ያሳያል የሚል ተስፋ አላቸው።

የዘርፉ ባለሙያዎች አዲሱ ግኝት ምናልባትም ከሰው ፍላጎት ጋር ለማጣጣም ገና ቢሆንም ወደፊት የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ኢንተርኔትን ተጠቅመው እንዴት ሊያድጉ እንደሚችሉ ማሳያ ነው ይላሉ።

በከሮናቫይረስ ምክንያት በዓለም ዙሪያ በርካቶች ቤታቸው እንዲሆኑ መገደዳቸው የኢንተርኔት አቅራቢ ድርጅቶችን ያላሰቡት እክል ውስጥ ከቷቸዋል። በርካቶች ከቤታቸው መሥራት መጀመራቸውና ለሥራቸውም ኢንተርኔት አንዱ አስፈላጊ ግብዓት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።

ባለሙያዎች በሚቀጥሉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ኢንተርኔት ከአሁኑ በላይ በጣም አስፈፈላጊ ይሆናል ይላሉ። ለዚህም ደግሞ ምክንያቱ ብዙዎች ከቤታቸው አሊያም ከመሥሪያ ቤት ውጭ ሆነው መሥራትን እንደ አማራጭ መውሰዳቸው አይቀርም፤ ይህ ደግሞ በተራው የኢንተርኔት ፍላጎትን ይጨምረዋል የሚለው ነው።

ተመራማሪዎቹ የተዘረጋ የኢንተርኔት ገመድን ተጠቅመው አዲስ ፍጥነት ማግኘታቸው እያሰወደሳቸው ነው።

እንደ ኔትፍሊክስ ለመሳሰሉ የፊልም ማሳያ ጣብያዎች ብቻ ሳይሆን፤ ለአሽከርካሪ አልባ መኪናዎች፣ ለሕክምና፣ ትምህርት እና የኢንተርኔት ንግድ አዲሱ ፈጣን ኢንተርኔት መፍትሄ ያመጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።