ማይክ ታይሰን ወደ ቦክስ መድረክ ሊመለስ ነው

ማይክ ታይሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቀድሞው የከባድ ሚዛን የቦክስ ሻምፒዮን ማይክ ታይሰን ወደ ቡጢው ዓለም ሊመለስ ነው።

ዝነኛው የቦክስ ተፋላሚ ማይክ ታይሰን ዕድሜው 54 ደርሷል። ወደ ቦክስ መፋለሚያ መድረክ የመመለሱ ዜና እያነጋገረ ነው።

ማይክ ታይሰን ለአጭር ደቂቃ በሚቆየው ፍልሚያ የሚገጥመው የአራት ጊዜ የቀድሞው የዓለም ሻምፒዮን የነበረውን ሮይ ጆንስ ጁኒየርን ይሆናል።

ሁለቱ ዝነኞች ለዚሁ ግጥሚያ የሚገናኙት መስከረም 12 ላይ በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ ውስጥ ነው።

ማይክ ታይሰን ለመጨረሻ ጊዜ ደንበኛ የቦክስ ግጥሚያ አደረገ የሚባለው እንደ አውሮፓዊያኑ በ2005 ነበር። በዚያ ውድድር ላይ በአየርላንዳዊው ተወዳዳሪ ኬቪን ማክብራይድ ክፉኛ ተደብድቦ ነበር። ይህም ታይሰን ካደረጋቸው 58 የቡጢ ፍልሚያዎች 6ኛው ሽንፈቱ ነበር።

በመጪው መስከረም ወር ታይሰንን የሚገጥመው ጆንስ ዕድሜው 51 ሲሆን በየካቲት 2018 ቡጢኛ ስኮት ሲግመንን ካሸነፈ ወዲህ ውድድር አድርጎ አያውቅም።

የካሊፎርኒያ ግዛት የአትሌቲክስ ኮሚሽን ይህ የቡጢ ፍልሚያ ሰዎች በተገኙበት እንዳይካሄድ ያዘዘ ሲሆን፤ ውድድሩ በክፍያ ብቻ በቀጥታ ይተላለፋል ተብሏል። ፍልሚያው 8 ዙሮች ይኖሩታል።

ማይክ ታይሰን የዓለም የከባድ ሚዛንን ሻምፒዮና የሆነው ገና በ20 ዓመቱ ነበር። ይህም የሆነው በፈረንጆቹ በ1986 ትሪቨር በርቢክን ማሸነፉን ተከትሎ ነው።

በቅርቡ ታይሰን በማኅበራዊ ሚዲያ የቦክስ ልምምድ ሲያደርግ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች መውጣታቸውን ተከትሎ ወደ ቦክስ ስፖርት ሊመለስ ነው የሚሉ ጉምጉምታዎች እዚያም እዚህም መሰማት ጀምረው ነበር።

በ2006 ታይሰን ተመሳሳይ አራት ዙር የቦክስ ግጥሚያ ከኮሪ ሳንደርስ ጋር ማድረጉ ይታወሳል። ያም የሆነው ማይክ ታይሰን በ2003 የገንዘብ ኪሳራ ገጥሞት ስለነበረና ገንዘብ ስላስፈለገው ነበር።

በቅርብ ጊዜ ደግሞ ማይክ ታይሰን ከኢቫንደር ሆሊፊልምድ ጋር ዳግም ሊገጥም ይችላል የሚሉ ወሬዎች መውጣት ጀምረው ነበር።

የ57 ዓመቱ ሆሊፊልድ ከቡጢ ራሱን ያገለለው በ2016 ነበር። ከታይሰን ጋር በ1990ዎቹ ሁለት ጊዜ በቦክስ መድረከረ ላይ ተገናኝተው ሁለቱንም ጊዜ ሆሊፊልድ ድል ቀንቶት ነበር።

ከዚህ ውስጥ በብዙዎች አእምሮ የቀረው በ1997 ታይሰን የሆሊፊልመድን ጆሮ መንከሱ ነበር።

የታይሰን የአሁኑ ተጋጣሚ ጆንስ ጁኒየር ስለ ውድድሩ በለቀቀው የቪዲዮ ማስታወቂያ "የታይሰንና የእኔ ወድድር የዳዊትና የጎሊያድ ፍልሚያ ነው የሚሆነው" ሲል ቀልዷል።