አቶ ልደቱ አያሌው በፖሊስ ተይዘው ወደ ቢሾፍቱ ከተማ ተወሰዱ

አቶ ልደቱ አያሌው

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት ፖለቲካኛው አቶ ልደቱ አያሌው በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፓርቲያቸው አስታወቀ።

አቶ ልደቱን ፖሊስ የያዛቸው በቅርቡ በቢሾፍቱ ከተማ ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት በማስተባበርና በመደገፍ ተጠርጥረው እንደሆነ አቶ አዳነ ታደሰ የኢዴፓ ፕሬዝዳንት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ዛሬ አርብ ረፋድ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ በፌደራል ፖሊስ ተይዘው መኖሪያቸው ወደሚገኝበት የቢሾፍቱ ከተማ እንደተወሰዱ ተገልጿል።

የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ የኦሮሚያ ፖሊስ አቶ ልደቱን ለመያዝ የመያዣ ትዕዛዝ ያወጣው ሐምሌ 03/2012 ዓ.ም እንደሆነና እስከ ዛሬ ሊያገኛቸው እንዳልቻለ መግለፁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ባቀረበው ክስ ምክንያት በአቶ ልደቱ ላይ የእስር ማዘዣው በቢሾፍቱ ከተማ ፍርድ ቤት የወጣ እንደሆነ አቶ አዳነ በመጨመር ገልጸዋል።

አቶ ልደቱ ነዋሪነታቸው ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ሲሆን፣ ዛሬ ረፋድ ላይ የፌደራል ፖሊስ ስልካቸው ላይ በመደወል እንደሚፈለጉ በመግለፁ፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ ቢሮ በመሄድ እዚያ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ፌደራል ፖሊስም ለሚፈልጋቸው የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ለማስረከብ እንደወሰዳቸው አቶ አዳነ ገልጸዋል።

አቶ ልደቱ የኢዴፓ መስራችና አባል አመራር ሆነው ለረጅም ዓመታት የቆዩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የድርጅቱ የብሔራዊ ምክር ቤት አባልና አብሮነት በሚባለው የፓርቲዎች ጥምረት ውስጥ የኢዴፓ አስተባባሪ ተወካይ ናቸው።

አቶ ልደቱ በአወዛጋቢው የ1997 ምርጫ ላይ ተሳትፈው በማሸነፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩ ሲሆን በራሳቸው ፖለቲካዊ ህይወትና በአገሪቱ ፖለቲካ ዙሪያ መጽሐፍትን ጽፈዋል።