በትግራይ ያለው ምርጫ የማካሄድ ፍላጎት ወዴት ያመራል?

አቶ አማኑኤል፣ አቶ ልደቱ እና አቶ ጀዋር
የምስሉ መግለጫ, አቶ አማኑኤል፣ አቶ ልደቱ እና አቶ ጀዋር

የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ስድስተኛው ዙር ምርጫን እንዲያስፈጽምለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።

ምንም እንኳ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትግራይ ክልል ለማካሄድ የጠየቀውን የክልላዊ ምርጫ ለማስፈጸም የሚያስችለው ሁኔታ የለም ቢልም የትግራይ ክልል የሚያቋቁመው አካል ምርጫውን እንደሚያስፈጽም የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ ለቢቢሲ አስታውቀዋል።

በትግራይ ክልል 6ኛው ምርጫ በተያዘለት ጊዜ እንዲካሄድ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሦስት የፖለቲካ ድርጅቶች ተሳታፊ የሚያደርጋቸው የጋራ ምክር ቤትና የምርጫ ተቋም እንዲቋቋም ለክልሉ መንግሥት በትናንትናው ዕለት ጠይቀዋል።

ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ ብሔራዊ ባይቶና ትግራይና የትግራይ ነጻነት ፓርቲ ትናንት [ሐሙስ] ባወጡት መግለጫ ክልላዊ ምርጫው ነሐሴ ወር መጨረሻ እንዲካሄድና ምርጫውን በሚመለከት የሚወጡ ሕጎችና መመሪያዎች የሚመራ የጋራ ምክር ቤት እንዲቋቋም ጠይቀዋል።

ይህም፤ በክልሉ ፍትሃዊና ነጻ ምርጫ እንዲካሄድ ይረዳል ብለዋል።

"የምርጫ ቦርድ እንደዚህ አይነት ውሳኔ ሊወስን እንደሚችል ምክር ቤቱ ያውቅ ነበር" ያሉት የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል፤ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ይህንን ውሳኔ ሲወስን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ "በበጎ አይቶት ምርጫውን የሚያስፈጽም ከሆነ" ምርጫውን እንዲያስተባብር ካልሆነ ግን "እንደተጀመረው ምርጫውን የሚያስተጓጉል ሥራ ከቀጠለ" በክልሉ የራሱ የሆነ የምርጫ አስተባባሪ አካልና የምርጫ ሕግ እንዲዘጋጅ ተወስኖ እንደነበር ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት "የምርጫ ቦርድ እንደማያስፈጽም ብቻ ሳይሆን ፖለቲካ ውሳኔ የሚመስሉ ሃተታዎችም በመግለጫው ተካቷል" ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትግራይ ክልል የሚካሄደውን ክልላዊ ምርጫ አላካሄድም ማለቱን በተመለከተ ቢቢሲ ያናገራቸው የባይቶና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ኪዳን አመነ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም ክልላዊ ምርጫው እንዲካሄድ እንደሚታገሉ አስታውቀዋል።

"እንደኛ ፓርቲ ግምገማ ቦርዱ ከዚያ ውጪ ፍላጎት እንደሌለው በተለያየ መንገድ በተለያየ መድረክ አረጋግጠናል" በማለት የቦርዱ ውሳኔ ካለው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታ የሚጠበቅ መሆኑን ይናገራሉ።

"ውሳኔው ግን ትክክል አይደለም፤ ባይቶና መደረግ አለበት [ብሎ ያምናል]። ህወሓት በሆነ ተአምር ምርጫውን ካላደረገ ግን የፖለቲካ ዋጋ እንዲከፍል ከሕዝባችን ጋር ሆነን የምንታገል ይሆናል" ብለዋል።

አቶ ኪዳነ ከትግራይ ክልል የሚጠብቁትንም ሲያስረዱም የክልሉ ምክር ቤት በፍጥነት በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ሁሉም የሚያምነው የክልሉ ምርጫ ቦርድ እንዲያቋቁም ይጠይቃሉ።

"ሁላችንም የተሳተፍንበትና ያመንበት ህግ [የምርጫ] እንዲያወጣ፤ ሕዝቡም አውቆ በኋላ ተጠያቂነትና ግልጽነት ያለው እንዲሆን ነው የምንፈልገው" ብለዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባል የሆኑት አቶ ጀዋር መሐመድ በበኩላቸው የግል አቋሜ ነው በማለት ለቢቢሲ በሰጡት ቃል "ትግራይም ሆነ የፌደራል መንግሥቱ ሕግን እየተላለፉ" መሆኑን ይገልጻሉ።

"መሆን የነበረበት ነገር ሁሉንም ያሳተፈ አገራዊ ውይይት ተካሂዶ፣ ምርጫ መሸጋገር አለበት ወይስ የለበትም። የሚሸጋገርስ ከሆነ የክልልም ሆነ የፌደራል መንግሥት እንዴት ነው በሥልጣን የሚቆየው። ምርጫው መቼ ነው የሚካሄደው የሚለው በውይይት መመለስ ነበረባቸው።"

አቶ ጀዋር አክለውም የፌደራል መንግሥት ለውይይት ዝግጁ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ደግሞ ከብልጽግና ውጪ በሌላ ፓርቲ እየተዳደረ ባለ ክልል የተለየ አቋም እንዲወሰድ ገፊ ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ።

መታየት ያለበት የክልልም መንግሥት ሆነ የፌደራል መንግሥት በምርጫ ላይ ሥልጣን እንዳላቸው ነው፤ የሚሉት አቶ ጀዋር።

"አንድ የክልል መንግሥት በክልሉ ምርጫ መቼና እንዴት መካሄድ እንዳለበት መወሰን ይችላል" በማለትም ምርጫ ቦርድ ደግሞ ምርጫውን ያስፈጽማል ሲል ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

"የፌደራል መንግሥት ምርጫውን አላስፈጽምም ማለቱ ሕጋዊ አይደለም" የሚሉት አቶ ጃዋር መሐመድ "ትግራይ ክልልም የራሴን ምርጫ አስፈጽማለሁ ማለቱ በቂ ሕጋዊ መሰረት አይኖረውም" በማለት ያስረዳሉ።

አቶ ጀዋር አክለውም የደፌደራል መንግሥቱ ምርጫውን አላስፈጽምም ካለ የትግራይ ሕዝብ ራሱ በመረጠው ፓርቲ የመተዳደር መብት ስላለው የክልሉ ምክር ቤት ሌላ መፍትሄ በመፈለግ የፌደራል መንግሥቱ ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ የምርጫውን ጊዜ እንዳራዘመ ሁሉ የትግራይም ክልል ሕጉን በመግፋት ምርጫ ማስፈፀም እንደሚችል ያብራራሉ።

"በጠቅላላው በትግራይና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ያለው ችግር ፖለቲካ እንጂ የምርጫ አለመሆኑን" የሚናገሩት አቶ ጀዋር ለዚህ ሁሉ መፍትሄ የሚሆነው ሁለቱም አካላት በውይይት ችግራቸውን ፈትተው ስምምነት ላይ ቢደርሱ መሆኑን ይናገራሉ።

አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው የምርጫ ቦርድ ውሳኔ የሚጠበቅ መሆኑን በመግለጽ በፌደራልና በትግራይ ክልል መካከል የተከሰተው ለአገሪቱ ህልውና አሳሳቢ መሆኑን ይናገራሉ።

የትግራይ ክልል መንግሥት አካሄድ ላይ ታይቷል ያሉትን ችግር የሚነቅሱት አቶ ልደቱ "ክልሉ ምርጫውን እንዲያካሂድ መጠየቅ የነበረበት የፌደራል መንግሥቱን ነበር" በማለት ነው።

"ምክንያቱም ምርጫ የማካሄድ ሕገመንግሥታዊ መብት ያለው ፌደራሉ ነው፤ በምርጫ ቦርድ አማካኝነት ማለት ነው" በማለት ውሳኔ መስጠትም የሚችለው የፌደራል መንግሥቱ እንጂ ምርጫ ቦርድ አለመሆኑን በማንሳት ይሞግታሉ።

የፌደራል መንግሥት ወይንም ሌሎች ክልሎች ምርጫ ባላካሄዱበት ሁኔታ፤ የትግራይ ክልል መንግሥት ምርጫ ሲያካሂድ የሚፈጠረው ነገር ምንድን ነው? በማለት የሚጠይቁት አቶ ልደቱ፤ የሚፈጠረው የሁለት አገር ሁኔታ ነው በማለት ለጥያቄያቸው ምላሽ እሰጣሉ።

አክለውም በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መካከል የተፈጠረው የምርጫ አካሄዳለሁ አላስፈጽምም እሰጥ አገባ፣ የቅራኔው ደረጃ የት እንደደረሰ ማሳያ ነው በሲሉ ተናግረዋል።

"በአንድ በኩል ምርጫውን በራሱ መንገድ ያራዘመ የፌደራል መንግሥትና ሌሎች ክልሎች አሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ያንን ሂደት አላምንበትም ብሎ ምርጫ ያካሄደ አንድ ክልል አለ ማለት ነው" ሲሉም ሁኔታውን ይገልጹታል።

እነዚህ ሁለት ኃይሎች አሁን የደረሱበት ሁኔታ የአገሪቱን ህልውና ምን ያህል አደጋ ላይ እየጣለው እንደሆነ ያሳየ ነው በማለትም ያብራራሉ።

አቶ ልደቱ አክለውም "ሁለቱ ኃይሎች የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከግንዛቤ አስገብተው፣ በኃላፊነት ስሜት ወደ መቻቻል፣ ወደ አብሮ መስራት፣ ወደ ጤናማ የሆነ ሰላማዊ ሁኔታ የመሄድ ፍላጎት እንደሌላቸው ያሳያል" ካሉ በኋላ "ሁኔታው በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ ችግሩ አገራዊ ይዘት ይኖረዋል" ብለዋል።