የኮሮናቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ 'የመተላለፍ ዕድሉ ዝቅተኛ ነው'

ጨቅላ ህጻን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮሮናቫይረስ ላለባቸው እናቶች አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ ከተደረገ በወሊድ ጊዜ ወደ ህጻናቱ የመተላለፍ እድሉ ዝቅተኛ ሊሆን እንደሚችል አንድ ጥናት አመለከተ።

አሜሪካ ኒው ዮርክ ውስጥ በሚገኙ ሦስት ሆስፒታሎች ኮሮናቫይረስ ካለባቸው እናቶች ከተወለዱ 120 ህጻናት ውስጥ አንዳቸውም በበሽታው አለመያዛቸው ተረጋግጧል።

ይህ ውጤት የተገኘው ህጻናቱ ከተወለዱ በኋላ ባለው ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከተወለዱ ከሁለት ሳምንታት በኋላ አንዳንዶቹ የእናታቸውን ጡት የመጥባት እድል ካገኙና በአንድ ክፍል ውስጥ አብረው ከቆዩ በኋላም ጭምር ነው።

ጥናቱን ያደረጉት ባለሙያዎች እንደሚሉት የተገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ተጨማሪ ሰፋ ያለ ሙከራዎች ማድረግ ያስፈልጋል።

በእርግዝናና በጡት ማጥባት ወቅት የበሽታውን ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ሁኔታን በተመለከተ ያለው መረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ የሚሰጠው ምክርም የተለያየ እንዲሆን አድርጎታል።

የዩናይትድ ኪንግደም ሐኪሞች እናቶች ጡት ማጥባት የሚፈልጉ ከሆነ አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ ተደርጎላቸው ልጆቻቸውን ጡት ማጥባትም ሆነ አንድ ክፍል ውስጥ መሆን ይችላሉ ብለዋል።

ባለሙያዎቹም ሆነ የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚሉት በኮሮናቫይረስ የመያዝ ስጋት የበለጠ ጡት ማጥባት ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል የቫይረሱን ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ዕድልን ለመቀነስ አዲስ የተወለዱ ህጻናት ለተወሰነ ጊዜ ከእናታቸው ተለይተው እንዲቆዩ የማድረግ ሃሳብን ተግባራዊ ለማድረግ እያሰበ ነው።

ኮሮናቫይረስ ያለባት እናት ከወለደችው ልጅ ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ እንድትቆይ የሚደረግና ጡት እንድታጠባ የሚፈቀድላት ከሆነ፤ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንድትጠቀምና በተደጋጋሚ እጇን መታጠብ እንደሚኖርባት በጥናቱ ተመልክቷል።

ጥናቱን የመሩት ዶክተር ክርስቲን ሳልቫቶሬ እንዳሉት "ጥናታችን ወረርሽኙ ያለባቸው እመጫት እናቶች ቫይረሱን ወደ ልጃቸው የማስተላለፍ ዕድላቸው በጣም ዝቅተኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ነገር ግን ሁኔታውን የበለጠ ለመረዳት አሁንም ሰፋ ያለ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ በዩናይትድ ኪንግደም የተደረገ ቅኝትን የመሩት ፕሮፌሰር ማሪያን ናይት እንደገለጹት ጥናቱ በአገሪቱ ያለውን መመሪያ የሚደግፍና የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ጨምረውም "በዩናይትድ ኪንግደም ከአንድ ሺህ በላይ ኮቪድ-19 ያለባቸው እናቶች የወለዱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ከ1 እስከ 2 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት ላይ ብቻ ነው ቫይረሱ የተገኘው። በሽታውም በህጻናቱ ላይ የከፋ ህመምን አላስከተለም።"

በአሜሪካ የተደረገው አነስ ያለ ጥናትም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምበል መጠቀመን የመሰሉ ቀላል የጥንቃቄ እርምጃ በመውሰድ የኮሮናቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ሁኔታ እንዳይከሰት ማድረግ መቻሉን ፕሮፌሰሯ ጠቅሰዋል።

የጥናቱ ውጤት የህጻናትና የአዋቂዎች ጤና ጉዳይ ላይ በሚያተኩረው የላንሴት የህክምና ሙያዊ መጽሔት ላይ ታትሟል።

ኮሮና