በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ ያለባት እናት ከበሽታው ነጻ የሆነ ልጅ ወለድች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ህክምና እያገኙ ባሉበት በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በኮሮናቫይረስ መያዟ የተረጋገጠች እናት ከኮቪድ-19 ነጻ የሆነ ልጅ መገላገሏን የጤና ሚንስቴር አስታወቀ።
የኮሮናቫይረስ በላብራቶሪ ምርምራ ተገኝቶባት በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የለይቶ ህክምና ማዕከል ውስጥ ክትትል እየተደረገላት የምትገኝ የ34 ዓመት እናት አርብ ግንቦት 14 ቀን ወንድ ልጅ በቀዶ ህክምና በሰላም መገላገሏ ተገልጿል።
ከህጻኑ የተወሰደው ናሙናም ጨቅላው ከቫይረሱ ነጻ መሆኑን አረጋግጧል ብሏል የጤና ሚንሰቴር። ሚንስቴሩ እናቲቱ ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ወንድ ልጀ በሰላም የመገላገሏ ዜና መስማት ተስፋ ሰጪ ነው ብሎታል።
እናቲቱ ልጇን በሰላም እንድትገላገል ለረዱ የህክምና ባለሙያዎች ጤና ሚንስቴር ምስጋናውን አቅርቧል።
እስካሁን ባለው መረጃ ኮቪድ-19 በእርግዝና፣ በምጥ ወይም ከምጥ በኋላ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድል አነስተኛ ቢሆንም፤ ከዚህ ቀደም ቫይረሱ ከሚገኘባቸው እናቶች የተወለዱ ህጻናት በቫይረሱ ተይዘው ተገኝተዋል ብሏል ጤና ሚንስቴር በፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ።
"ከወሊድ በኋላ በጡት ማጥባት ወቅት እና ዘወትር በሚኖር ንክኪ ቫይረሱ የመተላለፍ እድሉ ከፍተኛ ስለሆነ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመከራል።
እነዚህም ጥንቃቄዎች ጡት ከማጥባት ወይም ማንኛውም ንክኪ ከማደረግዎ በፊት እና በኋላ እጅዎትን በሳሙና እና በውሃ መታጠብ፣ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ የሚኖሩበትን ክፍል በቂ አየር እንዲኖረው እና እንዲናፈስ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል።
በተጨማሪም ወላጆች ለክትባት የሚኖራቸውን ቀጠሮ በአግባቡ መከታተል፣ በቂ የፀሐይ ብርሀን እንዲያገኙ ማድረግ፣ የተለያዩ በሽታዎች ምልክትን ማወቅ እና የህጻናትን ጤና ማስተዋል ይኖርባቸዋል ብሏል።














