ኮሮናቫይረስ፡ በህመሙ ለመጠቃት ምን ያህል የቫይረስ ቅንጣት መጠን ያስፈልጋል?

ጭምብል ያጠለቀች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰው ልጅ ደሴት አይደለም፤ ብቻችንንም ልንኖር አልተፈጠርንም። ያንንም በመገንዘብ ለሺዎች ዓመታት ሰዎች በአንድነት ኖረዋል።

በዓለም ታሪክ ውስጥ በዚህ ወቅት እየሆነ እንዳለው ማኅበራዊ ህይወት ጠንቅ ውስጥ ገብቶ አያውቅም። የኢትዮጵያ እናቶች እንደሚሉት "ከሰው የማያገናኝ፤ ማኅበራዊ ህይወት የሚጠላበት ክፉ ወቅት" ሰው ሰውን እንደሌባ የሚጠራጠርበት ዘመን።

አውቶብስ ውስጥ ለመግባት ተሰልፈን ተራችንን እየጠበቅን ድንገት የሚያስነጥስ ሰው ስናይ፣ ይሄ ሰውዬ ያስተላልፍብኝ ይሆን? አውቶብስ ውስጥ ልግባ ወይስ ዝም ብዬ ልሂድ? ብለን ራሳችንን እንጠይቃለን።

ምግብ ከቤት ውጭ መመገብ የከተሜነት ባህል በሆነባት ዓለም ወደ ምግብ ቤቶች መሄድ አለመሄድ በአሁኑ ወቅት ፈታኝ ሆኗል። ከዚህ ሁሉ በላይ የየእለት ጉዳያችንን ለማከናወን የሕዝብ ትራንስፖርት መጠቀም ለብዙዎች የሚፈሩትም ጉዳይ ከሆነ ከራረመ።

በተለይም በአሁኑ ጊዜ የኮሮናቫይረስን መዛመትን ለመግታት አገራት የወሰዷቸውን እርምጃዎች እያላሉ ባሉበት ሁኔታ ሕዝቡ ወደቀደመ ህይወቱ እየተመለሰ ነው።

የተለያዩ ማኅበራዊ ህይወታቸውንም ለመመለስ ደፋ ቀና እያሉ ቢሆንም፤ ሠርግ፣ ቀብር፣ ተሰባስቦ መመገብና የመሳሰሉት የቫይረሱን መዛመት ሊጨምሩት ይችላሉ የሚል ስጋትን አዝለዋል። በተለይም ሁለተኛ ዙር ወረርሽኙኝ ሊያገረሽ ይችላል የሚል ፍራቻን አንግሷል።

የሰውነትን በሽታዎችን የመከላከል አቅም ላይ ጥናትን ያደረጉት የሥነ ህይወት (ባዮሎጂ) ረዳት ፕሮፌሰር ኤሪን ብሮሜጅ የኮሮናቫይረስ ስጋትን ልንቀንስ የምንችልበት እንዲሁም እንዳይዘን የምናደርግበት ሁኔታን በተመለከተ ቢቢሲ ምክር እንዲለግሱ ጠይቋቸዋል።

በማሳቹሴትስ ዳርት ማውዝ ዪኒቨርስቲ ስለ ወረርሽኝና ተላላፊ በሽታ የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር ኤሪን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በቅርበት ተከታትለውታል።

ራሳቸውን በበሽታዎች ላይ ልሂቅ አድርገው የማይቆጥሩት ፕሮፌሰሩ በአንፃሩ ራሳቸውን ሳይንሳዊ መረጃዎችን አቀባይ ብለው ነው የሚጠሩት።

በኮሮናቫይረስ ስጋቶች ላይ የፅሁፍ ስራዎችን ያበረከቱ ሲሆን አንደኛው ፅሁፋቸውም 16 ሚሊዮን ጊዜ ተነቧል።

ወደቀደመ ህይወታችን ለመመለስ በምናደርገው ጥረት ውስጥ እንዴት ደኅንነታችንን መጠበቅ እንደምንችል የለገሷቸው ምክር እነሆ።

የሙዚቃ ዝግጅት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰዎች የት ነው የሚታመሙት?

ፕሮፌሰር ኤሪን እንደሚሉት አብዛኛው ሰው በቫይረሱ የሚጠቃው በቤቱ ውስጥ ሲሆን፤ ይህም ከሩቅ ሰው ሳይሆን ከቤተሰብ አባላት ጋር በሚደረግ ንክኪና ግንኙነት ነው።

ከቤታችን ውጭ ስንሆንስ? በየቀኑ አየር ለመቀበል በምንራመድበት ወቅት? ወደፓርኮች በምንሄድበት ወቅትስ? አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ያለ ፊት ጭምብል የሚሮጡ ሰዎች ቫይረሱን ሊያስተላልፉብን ይችሉ ይሆን? የሚሉት በርካታ ጥያቄዎች በአእምሯችን ይመላለሳሉ።

ፕሮፌሰሩ ለዚህ ምላሽ አላቸው የሚተላለፍበት አጋጣሚ ትንሽ ነው ይላሉ።

"ከቤት ውጭ ባሉ ቦታዎች በምንተነፍስበት ወቅት ትንፋሻችን በአጭር ጊዜ ነው በንኖ የሚጠፋው። በአየር ላይ የመቆየት እድል የለውም" ይላሉ።

ይህ ማለት በቫይረሱ ለመያዝ ረዘም ያለ ጊዜ አይኖርም ማለት ነው።

"በቫይረሱ ለመያዝ ማጥቃት የሚችል የቫይረሱ መጠን መኖር አለበት። ከዚህ ቀደም በመርስና ሳርስ ተላላፊ በሽታዎች ላይ በተደረገ ጥናት 1 ሺህ መጠን ያለው የቫይረስ ቅንጣቶች ያስፈልጋሉ። ከዚህም በመውሰድ ለኮሮናቫይረስም አንድ ሺህ የቫይረስ ቅንጣቶች እንደሚያስፈልጉ ተረድተናል" በማለት በፅሁፋቸው ላይ አትተዋል።

ጭምብል ሳታደርግ የምትሮጥ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ይህ ቁጥር አሁንም ቢሆን አከራካሪ ሲሆን በተለያዩ ሙከራዎችም የሚወሰን አይደለም። ሆኖም ግን ቫይረሱ እንዴት እንደሚተላለፍ ጠቃሚ መረጃን ይሰጣል።

ዋናው ጉዳይ የተጠቀሱት የቫይረሱ ቅንጣቶች ቁጥር ላይ በተለያየ መንገድ ከተጠቀሰው አንድ ሺህ ቅንጣቶች መድረስ ይችላል።

"በአንድ ትንፋሽ አንድ ሺህ የቫይረሱን ቅንጣቶች ሊቀበሉ ይችላሉ ወይም በአስር ትንፋሽ መቶ የቫይረሱን ቅንጣቶች እንዲሁም ሌላ አማራጭ በመቶ ትንፋሾች አስር የቫይረሱን ቅንጣቶች ሊሆን ይችላል። እያንዳንዷ አጋጣሚ ግን በቫይረሱ ወደመጠቃት የሚያመሩን ናቸው" በማለት ያስረዳሉ።

በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር አጭር ጊዜ ካሳለፍን ወይም ያለ ጭምብል አካላዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ያገኘናቸው ሰዎች በቫይረሱ የምንጠቃበትን የቫይረስ ቅንጣት መጠን ማስተላለፍ አይችሉም።

ስለዚህ መጠንቀቅ ያለብን ከምን አይነት ጉዳዮች ነው?

የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ

ሳልም ሆነ ማስነጠስ በተለያየ ደረጃ በሽታውን በከፍተኛ ሁኔታ ያስተላልፋሉ።

እንደ ፕሮፌሰሩ ከሆን አንዴ በሚሳልበት ወቅት በአማካኝ ሦስት ሺህ ጠብታዎች የይረጫሉ።

ጠብታዎች ከበድ ያሉ ሲሆኑ በአንዴም ወደ መሬት ይንጠባጠባሉ፤ የተወሰኑት ደግሞ በአየር ላይ ይቀሩና በነፋስ አማካኝነት የመጓዝን እድል ያገኛሉ።

ነገር ግን ድንገት በአሳንሰር (ሊፍት) ውስጥ ሆነው አንድ ግለሰብ ከመሳል ይልቅ ቢያነጥስ በቫይረሱ የመያዝ እድልዎ አስር እጥፍ ይጨምራል።

በአንድ ማስነጠስ በአማካኝ ሰላሳ ሺህ ጠብታዎች ይወጣሉ፤ በክብደታቸውም ቀላል ስለሆኑ ረዥም ርቀትን የመጓዝ አቅማቸውም በጣም ከፍተኛ የሚባል ርቀትን መሸፈን የሚችሉ እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።

"በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ቢያነጥስ ከሰውየው የሚወጣው የቫይረሱ ቅንጣት ሁለት መቶ ሚሊዮን ይደርሳልም" በማለትም ምሁሩ በፅሁፋቸው ላይ አስፍረዋል።

"እናም በቫይረሱ የተያዘ ሰው ጋር አንድ ላይ ተቀምጠው እያወሩ ፊት ለፊት ቢያነጥስብዎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቫይረሱ ቅንጣቶች ከመለቀቃቸው አንፃር የሚጠቁበትም ዕድል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችሉ ማወቅ ይገባዎታል።"

ድንገት እንኳን በቫይረሱ የተጠቃው ሰው አስነጥሶ ወደ ሌላ ቦታ ቢሄድ እንኳን ከመጠቃት አምልጠዋል ማለት አይደለም፤ አንዳንድ ጠብታዎች በአየር ላይ ለደቂቃዎች የመቆየት እድል አላቸው። እዚያ ክፍል ሰውየው በሌለበት ወቅት ቢገቡ ሊጠቁ ይችላሉ።

ባርኔጣ አድርጎ መንገድ የሚያቋርጥ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምልክት የማያሳዩ አስተላላፊዎች

በቫይረሱ የተጠቁ ህሙማን ምልክቶቹን ለአምስት ቀናት ላያሳዩ ይችላሉ፤ ሆኖም በሽታውን ያስተላልፋሉ። አንዳንዶቹም ጭራሽ ምልክት እስከ መጨረሻው ላይታይባቸው ይችላል።

ከዚህም በላይ በትንፋሽም ቫይረሱ ወደ ከባቢው ይለቀቃል። ግን ምን ያህል?

በአንዴ የምንተነፍሰው ከ50 አስከ 5000 ጠብታዎች ይኖሩታል። አብዛኛዎቹ ጠብታዎች በፍጥነት መሬት ላይ ያርፋሉ።

በተለይም በአፍንጫችን በምንተነፍስበት ወቅት የጠብታዎቹ መጠን ይቀንሳሉ።

"በምንተነፍስበት ወቅት ተጣርቶ ስለሆነ የሚወጣው የቫይረሱም ቅንጣቶች ይቀንሳሉ። ከዚህም በተጨማሪ በምንተነፍስበት ወቅት ወደውጭ መግፋት የሚያስችለን ከፍተኛ ኃይል ስለሚያጥረን፤ ከታችኛው የመተንፈሻ አካላችን የቫይረሱ ቅንጣቶች አይወጡም" በማለት ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ይሄ ጉዳይ በጣም ጠቃሚ ግኝት ነው፤ ምክንያቱም የኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠራቅሞ የሚገኘው በታችኛው የመተንፈሻ አካላችን ውስጥ በሚገኙ ህብረ ህዋሳት ነው።

ሆኖም አንድ ሰው በሚተነፍስበት ወቅት ምን ያህል የኮሮናቫይረስ ቅንጣቶች እንደሚለቀቁ መረጃ የለም፤ ሆኖም ፕሮፌሰሩ በጉንፋን ላይ የተደረገ ጥናትን ጠቅሰው ከ3 እስከ 20 ሊሆን ይችላል ይላሉ።

ለኮሮናቫይረስም በተመሳሳይ መልኩ የሚሰራ ከሆነ አንድ ህመምተኛ ሃያ የቫይረስ ቅንጣቶችን የሚተነፍስ ከሆነ በቫይረሱ ለመያዝ ሰውየው ያለማቋረጥ ለአምሳ ደቂቃ ሊተነፍስብን ይገባል። በዚህ መሰረት ነው አንድ ሺህ ያህል የቫይረሱ ቅንጣቶች ላይ መድረስ የሚቻለው።

ስለዚህ ምልክት የማያሳዩ ሰዎች ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ መሆን በሽታው ላይተላለፍ ይችላል።

በመጠጥ ቤት ውስጥ የሚያወሩ ሁለት ግለሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መናገር የጠብታዎቹን መጠን በአስር መጠን የሚጨምረው ሲሆን በደቂቃም 200 ያደርሰዋል።

መዝፈን እንዲሁም ባልተገባ መንገድ እየተወናጨፉ መጮህ በአየር ላይ የሚፈናጠሩትን የጠብታዎች መጠን እየጨመረው ይሄዳል።

"በመድረክ ላይ ሆነው በሚጮሁበት እንዲሁም በሚዘፍኑበት ወቅት ጠብታዎቹ በቀጥታ ወደ ሳንባ ነው የሚገቡት" በማለት ይናገራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ እነዚህም ጠብታዎች የሚወጡት በከፍተኛ ሁኔታ በቫይረሱ ከተጠቁ ህብረ ህዋሳት ነው።

"ለመጮህ ከፍተኛ የሆነ ኃይል ስንጠቀም፤ ጠብታዎቹም የሚወጡት በከፍተኛ ሁኔታ የቫይረሱን መጠን ከያዙት ህብረ ህዋሳት ነው" ይላሉ።

ምንም እንኳን በዚህ መንገድ የቫይረሱ የመተላለፍ ሁኔታ በጣም ዝቅተኛ ቢሆንም፤ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከቤት ውጭ ቫይረሱን የሚያዛምቱት የኮሮናቫይረስን ምልክቶች የማያሳዩ ናቸው።

የሚዘፍኑ ታዳጊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትኞቹ አካባቢዎች የበለጠ አስጊ ናቸው?

ግልፅ በሆነ መንገድ ከቫይረሱ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው የጤና ባለሙያዎች በስጋት የአንበሳ ድርሻውን ይይዛሉ።

አንዳንድ አካባቢዎችም እንዲሁ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ ተይዘውበታል።

በተለያዩ መርከቦች፣ የቢሮ ስብሰባዎች፣ ስፖርታዊ ዝግጅቶች፣ የልደት ድግሶች እንዲሁም የቀብር ሥርዓቶች ፕሮፌሰሩ ከሚጠቅሷቸው መካከል የተወሰኑት ናቸው።

በእነዚህ አጋጣሚዎች ድንገት የታመመ ሰው ካለ በርካታ ሰዎች ተሰባስበው ረዘም ያለ ጊዜን ማሳለፋቸው በቫይረሱ የመጋለጣቸውን ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምረዋል።

"ምንም እንኳን አስራ አምስት ሜትር ርቀት ላይ ቢገኙም፣ በአየር ላይ የሚገኘው ቫይረስ ካሉበት ለመድረስ ሩቅ ቢሆንም፤ ረዘም ያለ ጊዜ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቫይረሱ የመጠቃት ሁኔታዎን ይጨምረዋል" ይላሉ።

ወደ ሥራም በምንመለስበት ጊዜ አንዳንድ የሥራ አይነቶችም በተለየ መንገድ ስጋት ይኖራቸዋል።

የተለያየ ክፍል የሌላቸው፣ አዳራሽ በሚመስል ሁኔታ የተሰሩና አየር መተላለፍ የማይችልባቸው ቢሮዎች የሚሰሩ ሰዎች ፈታኝ ሁኔታ ይገጥማቸዋል።

ፕሮፌሰሩ እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱትም በደቡብ ኮሪያ በአንድ ቢሮ ውስጥ ከሚሰሩ 216 ሠራተኞች መካከል 94ቱ በቫይረሱ መጠቃታቸውን ነው። በቫይረሱ የተጠቁትም አብዛኛው አንድ ሰፋ ያለ ቢሮን የሚጋሩ ናቸው።

የጥርስ ሐኪሞች ብዙ ባይባሉም ለኮሮናቫይረስ ስጋት የተጋለጡ ናቸው።

"የጥርስ ሐኪሞች የሥራቸውን ቦታ እንደገና ሊያጤኑት ይገባል። በዋነኝነት የሚጎዱት የጥርስ ሐኪሞቹ ናቸው፤ ህመምተኞቹ አይደሉም። ህመምተኞቹ በቀላሉ ወደ ሐኪሞቹ ቫይረሱን ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ምክንያቱም ሃኪሞቹ ተጠግተው ጥርስ ይቦረቡራሉ፣ ከአፍ የሚወጣውን ፈሳሽ ሁሉ ያጸዳሉ። ዶክተሮቹ የራሳቸውን ጤንነት ቢጠብቁም የህመምተኞቻቸውን ሁኔታ ማወቅ ግን አይችሉም" ይላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ መምህራንም በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ናቸው።

"በእድሜያቸው ጠና ያሉ መምህራንና ፕሮፌሰሮች በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች በአንድ ክፍል ውስጥ ያስተምራሉ። እነዚህን የሥራ አይነቶች ደኅንነታቸውን የተጠበቀ ለማድረግ ኮሮናቫይረስን ከግምት ውስጥ በማስገባት መከለስ ያስፈልጋል" ብለዋል።

ከቤት ውጭና ቤት ውስጥ

እስካሁን በቫይረሱ ከተያዙት መካከል ከቤት ውጭ የተያዙት በቁጥር በጣም ትንሽ ናቸው። ነፋስ፣ አየር፣ የፀሐይ ብርሃን፣ ሙቀትና እርጥበት ቫይረሱን በአየር ላይ ላያቆዩት ይችላሉ።

ስለዚህ አካላዊ ርቀታችንን ጠብቀን፣ ከሰዎች ጋር የምናሳልፈውን ጊዜ በመቀነስ ስጋቱንም ልንቀንስ እንችላለን።

ሆኖም አንዳንድ ከቤት ውጭ የሚደረጉ መስተጋብሮች አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ።

ሰዎች ተሰብስበው የሚያወሩበት፣ የሚዘፍኑበት እንዲሁም የሚጮሁበት አጋጣሚ ከሆነ ስጋቶች ይጨምራሉ።

በቤት ውስጥ የሚደረጉ አካላዊ ርቀቶች ከጊዜ በኋላ እየቀሩ ይመጣሉ።

በዚህም ሁኔታ ዝቅተኛ አየር የሚዘዋወርበት ሁኔታ ካለ ደግሞ ስጋቱን ከፍ ያደርገዋል።

ሆኖም የተለያዩ እቃዎችን ለመሸመት በምንወጣበት ጊዜ ብዙ በመደብሮች ላይ የምናሳልፈው ጊዜ የተወሰነ ከሆነ ስጋቱም በጣም ዝቅተኛ ይሆናል።

ጠረጴዛዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስጋቶችን መገምገም

የኮሮናቫይረስ መመሪያዎች እየላሉ ባሉበት በአሁኑ ወቅት እንቅስቃሴዎቻችን ምን አይነት ስጋት ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚለውን መገምገም አለብን።

የትኛውም ቢሮም ይሁን ቤት ውስጥ በምትሆኑበት ወቅት ቦታው ያለውን ስፋት፣ ያሉትን ሰዎች ብዛት እንዲሁም ምን ያህል ጊዜ በዚያ ቦታ እንደምናሳልፍ ልናስብበት ይገባል።

"አየር የሚተላለፍበትና፣ ጥቂት ሰዎች ያሉበት ቦታ ከሆነ ስጋቱ ዝቅተኛ ነው። ግን ቢሮው ሰፊና ብዙዎች የሚጋሩት ከሆነ ስጋቱን እንደገና ልናጤን ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ የሥራዎ ሁኔታ ፊት ለፊት መነጋገር እንዲሁም ጮክ ብሎ መነጋገር ያለበት ከሆነ ስጋቱ ስለሚልቅ በከፍተኛ ሁኔታ ልናስብበት ይገባል።"

"ምንም እንኳን ያተኮርኩት ትንፋሽ፣ ማስነጠስና ሳል ላይ ቢሆንም ሌላ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን ጠብታዎቹ የሚያርፉበትን ቦታ ነው። ሁልጊዜም ቢሆን እጃችንን በተደጋጋሚ መታጠብ፣ ፊታችንን መንካት ማቆም አለብን" በማለት ጽፈዋል።

በመጨረሻም ለልደታችን ተብሎ የተዘጋጀው ኬክ ላይም ሻማ ማጥፋት እንድናቆምም መክረዋል።

ኮሮና