የልጄ ገዳይ ኮሮናቫይረስ እንዳይዘው ከእስር ልቀቁልኝ ያሉት አርጀንቲናዊ እናት

የሲሊቪያ ልጅ አሌሆ ሁናው

የፎቶው ባለመብት, Alejo Hunau

የምስሉ መግለጫ, የሲሊቪያ ልጅ አሌሆ ሁናው

ሲልቪያ ኦንቲቫሮ የተባሉ አርጀንቲናዊት፤ የአስም ታማሚ የሆነው የልጃቸው ገዳይ በኮሮናቫይረስ እንዳይያዝ፣ ከእስር ቤት እንዲለቀቅ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለባለሥልጣኖች ጽፈዋል።

ሲልቪያ ከሁለት ወር በፊት የልጃቸው ገዳይ ከእስር ቤት ለመለቀቅ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ እንዲሆን አቤቱታ አሰምተው ነበር። ሆኖም ግን ወቅታዊው ሁኔታ ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል።

“እጅግ ተበሳጭቼበታለሁ፤ በጥላቻ ተሞልቼም ነበር፤ ቢሆንም እንዲሞት አልፈልግም” ሲሉ በደብዳቤያቸው ተማጽነዋል።

ባለፈው ማክሰኞ የአርጀንቲናው ፕሬዘዳንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ ታራሚዎች ከእስር ቤት ተለቀው በቤታቸው የቁም እስር እንዲገቡ የቀረበውን ሐሳብ ተቀብለዋል።

የፕሬዘዳንቱ ውሳኔ ፍትህ ያዛባል የሚሉ ወገኖች፣ በተቃራኒው ታራሚዎች ይፈቱ የሚሉም አሉ።

ታራሚዎች በተጨናነቁባቸው እንዲሁም ንጽህናቸው ባልተጠበቀ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ኮሮናቫይረስ በፍጥነት ሊሰራጭ ይችላል በሚል ስጋት፤ ባለፉት ሳምንታት በማረሚያ ቤቶች ተቃውሞ ሲካሄድ ነበር።

“ታራሚዎች ምን ያህል እንደፈሩ መገመት እችላለሁ”

የሲሊቪያ ልጅ አሌሆ ሁናው የተገደለው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2004፣ በሜንዶዝራ ግዛት ነበር። ገዳዩ ዲዬጎ አርዱኢኖ የ16 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።

ባለፈው ማክሰኞ ማሪያና ጋርዲ የተባሉ ዳኛ፤ ዲዬጎ አስም ስላለበት ለበሽታው ሊጋለጡ ከሚችሉ 400 ታራሚዎች አንዱ ነው ብለው ነበር።

ሲልቪያ በጻፊት ግልጽ ደብዳቤ፤ የቁም እስርን እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

“ወረርሽኝ ገጥሞናል፤ ማረሚያ ቤቶች ደግሞ የተጨናነቁ ናቸው፤ ታራሚዎች ምን ያህል እንደፈሩ መገመት እችላለሁ” ብለዋል።

ቲኤን ለተባለ የቴሌቭዝን ጣቢያ፤ ዲዬጎን ከእስር አለመፍታት እንደ ሞት ፍርድ ይቆተራል ሲሉ ተናግረዋል። ይህንን እንደማይቀበሉም አክለዋል።

ሲልቪያ ከ1976 እስከ 1983 በነበረው ወታደራዊ አገዛዝ ስር ለሰባት ዓመታት የፖለቲካ እስረኛ ነበሩ።

ማረሚያ ቤት የማሰላሰያ ጊዜ እንደሰጣቸው የሚናገሩት እናት፤ ዲዬጎ ከዚህ ቀደም ሊፈታ ሲል የተቃወሙት በቂ ማሰቢያ ጊዜ ማግኘቱንና የተሻለ ስብእና ማዳበሩን እርግጠኛ ስላልሆኑ ነበር።

ጋዜጠኛና የሜንዶዝና አስተዳደር አማካሪ የነበረው ልጃቸው ቤቱ ውስጥ በወይን ጠርሙስ ተመቶ ነበር ሕይወቱ ያለፈው።

በሊማ ከተማ ማረሚያ ቤት በተካሄደ ተቃውሞ ዘጠኝ ሰዎች ሞተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ተቃውሞ በማረሚያ ቤቶች

በሊማ ከተማ ማረሚያ ቤት በተካሄደ ተቃውሞ ዘጠኝ ሰዎች ሞተዋል። በወቅቱ ሁለት ታራሚዎች በኮቪድ-19 ሳቢያ መሞታቸውን ተከትሎ ታራሚዎች ለማምለጥ ሞክረው እንደነበርበ እስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች ተገልጿል።

የቀድሞው የቺሊ ፕሬዘዳንትና የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ሚሼል ባቼሌት የላቲን አሜሪካ ማረሚያ ቤቶች ፅዱ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ብዙም አደገኛ ያልሆኑ ታራሚዎች እንዲፈቱም ጥሪ አቅርበዋል።

ቺሊ እና ኮሎምቢያ በሺዎች የሚቆተሩ ታራሚዎችን ፈተዋል። ባለፈው ሳምንት የሜክሲኮ ምክር ቤት ታራሚዎች እንዲፈቱ ውሳኔ አስተላልፏል።

በተቃራኒው ኤል ሳልቫዶር የአመጽ ቡድን አባሎች ወረርሽኙን ሰበብ በማድረግ ከማረሚያ ቤት ለመውጣት እየሞከሩ ነው ብላለች።

ባለፈው እሮብ አርጀንቲና ውስጥ ሰብአዊ መብት በመጣስ ታስሮ የነበረው የ 70 ዓመቱ ካርሎስ ካፕዲቪላ ተለቆ ወደ ቁም እስር መግባቱ ውዝግብ አስነስቷል።

ደም ግፊትን ጨምሮ ሌሎችም ህመሞች ስላሉበት ለኮሮናቫይረስ እንዳይጋለጥ ተብሎ መፈታቱ ተገልጾ ነበር።

ኮሮና