በአፍሪካ በኮቪድ-19 የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን ምን ያህል ይታመናል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደቡብ አፍሪካ የኮሮናቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየተዛመተ ይገኛል። በአገሪቱ ውስጥ ለቫይረሱ ስርጭት መስፋፋት ሰበብ የሆኑና ሌሎች አፍሪካውያን ሊማሩባቸው የሚችሏቸው ነጥቦች ግን አሉ።
ቁጥሮች ሁሉን አይናገሩም
ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ከሚገኙ አገራት ሁሉ የተሻለ የመረጃ አሰባሰብና አደረጃጀት ልምድና ተሞክሮ አላት። ግን ቁጥሮችን ማመን ከባድ ነው። ቁጥሮችን ብቻ ሳይሆን እንደማሳያ የሚወሰዱ መረጃዎችን ማመኑም አዳጋች ነው።
አንዳንድ ታዛቢዎች በአገሪቱ በኮቪድ-19 ተይዘው የሞቱ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን በማየት ብቻ የአገሪቱን ስኬት ለማንቆለጳጰስ ይሮጣሉ። ይህ የሆነው በአገሪቱ ውስጥ የወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ ስለሆነ ነው? ወይስ አፍሪካውያን የተለየ የመከላከል ብቃት፣ ተፈጥሮ ወይም ሌላ ምስጢር ስላላቸው ነው?
መልሱ አጭርና ግልጽ ነው። አይደለም። ደቡብ አፍሪካ በኮቪድ-19 ምክንያት እየተጋፈጠች ያለውን ሞት ለመናገር ጊዜው ገና ነው።
ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ ትልልቅ ሆስፒታሎች በኮቪድ-19 ተይዘው የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከጣልያን እና ዩናይትድ ኪንግደም ጋር ሲነጻጸር እጅጉን ተቀራራቢ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነገር ግን ይህንን ቁጥር ወደ ሆስፒታል መጥተው ሕክምና እርዳታ ከሚፈልጉ ሰዎች ውጪ መመልከት በተለያዩ አገራት የተለያየ መረጃ ይሰጣል። ይህ ደግሞ የሆነበት ምክንያት አገራት በመሰረታዊነት በኮቪድ-19 ምክንያት የተከሰተ ሞትን ሲመዘግቡ የተለያየ መስፈርትና ስልት ስላላቸው ነው።
ፕሮፌሰር ሻቢር ማድሂ በዊትዋተርስራንድ ዩኒቨርስቲ የክትባት ባለሙያ ናቸው ስለሞት ምዝገባ ሲያስረዱም "እርባና የለውም" በማለት ነው።
ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው በአህጉሪቱ በአጠቃላይ በጣም አነስተኛ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን በመጥቀስ ለማነፃፀርም ሆነ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ እንደማይቻል በመግለጽ ነው።
የሆስፒታል ፍራቻ
ደቡብ አፍሪካውያን ተመራማሪዎች ባሳተሙት አንድ ጥናት ላይ በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉ የሚጠረጠር ነገር ግን ያልተመዘገቡ 17 000 ሞቶች ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።
ይህ ጥናት እንደሚያሳየው ዜጎች ወደ ሕክምና ተቋማት ለመሄድ ያላቸው ፍራቻ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ተቋማቱ በቅርብ አለመገኘታቸው ተጨምሮበት ሳይታወቁ ለሚከሰቱ ሞቶች ሰበብ ሆኖ ሊሆን ይችላል ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ይህም ማለት ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች በቤታቸው ውስጥ ያለምንም ሕክምና እርዳታ እየሞቱ ነው ማለት ነው።
በደቡብ አፍሪካ ኮቪድ-19 ከተከሰተ በኋላ ቲቢ ለመመርመር ወደ ሆስፒታል የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር በግማሽ፣ ለክትባት የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ደግሞ በ25 በመቶ ቀንሷል።
የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት
በደቡብ አፍሪካ ፖርት ኤልዛቤጥ በባለሃብቶች ትልቅ የኮሮናቫይረስን ለማከም የሚውል "የመስክ ሆስፒታል" ተገንብቷል። ነገር ግን ባለፉት ሳምንታት ካሉት 1200 አልጋዎች 30 ብቻ ነው በሕሙማን ተይዞ የነበረው። ለዚህ ደግሞ እንደምክንያት የተጠቀሰው የኦክስጅን አለመኖርና የባለሙያዎች እጥረት ነው።
ፕሮፌሰር ማድሂ እንዲህ አይነት ሆስፒታሎች ሲገልጿቸው "አእምሮ የሌላቸው" ይሏቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ይህ ግን በደቡብ አፍሪካ ብቸኛው ማሳያ አይደለም። በርካታ ሆስፒታሎች የባለሙያ እጥረትና የኦክስጅን አለመኖር የኮቪድ-19 ህሙማንን በማከሙ ረገድ እግር ተወርች እንዳሰራቸው ይናገራሉ። ለዚህም በጎ ፈቃደኞችንና ለጋሾችን በመማፀን ያለውን እጥረት ለማሟላት እየጣሩ ነው።
"ኦክስጅን ዋናው ነገር ነው" የሚለው በእነዚህ ሆስፒታሎች የሚሰራው ዶክተር፣ የባለሙያም ሆነ የኦክስጅን እጥረት እንዳለ እየታወቀና ለመግዛትም ሆነ ለመቅጠር ሙከራ ሳይደረግ፣ ለጤና ተቋማቱ ተጨማሪ የሕሙማን አልጋዎች ማስገባትና መዘርጋት የገንዘብም ሆነ የጊዜ ብክነት መሆኑን ያስረዳል።
የኮሮናቫይረስ ወጀብ አብሮን ነው
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ላይ እንደጠቀሱት "አሁንም ወጀቡ አብሮን አለ።"
ይህ ንግግር ኮሮናቫይረስ ገና ድል አለመመታቱን ለመግለጽ የተጠቀሙበት ዘይቤ ነው። የፕሬዝዳንቱ ንግግር ለደቡብ አፍሪካም ሆነ ለቀሪው የአህጉሪቱ ክፍሎች እውነትነት እንዳለው የሚጠቅሱ ባለሙያዎች ምክራቸውን ይለግሳሉ።
ክትባት ባልተገኘበት፣ ተፈጥሯዊ የወል መከላከያ ባልጎለበተበት ወይንም መሰረታዊ የባህሪ ለውጥ ባልመጣበት ሁኔታ ደቡብ አፍሪካ ኮሮናቫይረስን መመልከት ያለባት እንደ ቲቢና ኤች አይቪ አብሯት እንደሚቆይ ነው።
ይህም ልክ ሁለቱን በሽታዎች ለማከም፣ ለመቆጣጠር የወሰደቻቸውን እርምጃዎችና የዘረጋቻቸውን ሥርዓቶች ለመተግበር ያስችላታል ይላሉ።
ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው ቫይረሱ ለረዥም ጊዜ አብሮን እንደሚቆይ በማንሳት ነው።
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች በየትኛው ስፍራ፣ መቼና በማን መደረግ አለባቸው የሚለው ወረርሽኙ ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ ሲያነጋግር ነበር። አሁን ግን በርካታ አገራት ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች መሸፈኛዎቹ መደረግ እንዳለባቸው ደንግገዋል። ደቡብ አፍሪካውያ ይህንኑ መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእርግጥ የደቡብ አፍሪካ ምግብ ቤቶች፣ ሆቴሎችና መዝናኛ ስፍራዎች የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት በሚል መንግሥት በጣለው ገደብ የተነሳ መጠጥ እንዳይሸጡ መከልከላቸው አስቆጥቷቸዋል። ባለፈው ሳምንትም የምግብ ቤቶች ባለቤቶች ባዶ ወንበሮቻቸውን ይዘው አደባባይ ለተቃውሞ ወጥተው ነበር።
አሁንም ቢሆን ግን ሃኪሞች በየትኛውም ስፍራ ሁል ጊዜና በአግባቡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን ማድረግ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል እንደሚረዳ ይመክራሉ።
በደቡብ አፍሪካ የተስተዋሉ ሌሎች ሁለት ነገሮች አሉ። የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመከላከል ትልልቅ ሆስፒታሎችና ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ አነስተኛ ድርጅቶችና የግለሰቦች ጥረትም ወሳኝ በመሆናቸው ሊደገፉ እንደሚገባ ነው።
ሌላው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚታዩ ሙስናዎችን ማጋለጥ ቁልፍ ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ተስተውሏል። በዚህ ወቅት የመከላከያ ቁሳቁስ ግዢ፣ የእርዳታ አቅርቦት ላይ የሚኖሩ ሙስናዎችን የመከላከል ሥራውንም ሆነ የቫይረሱ ስርጭት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል ሲሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

















