ኮሮናቫይረስና የወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ፈተና

የፎቶው ባለመብት, ESTELLE LUCAS
ዘመኑ አካላዊ ርቀት መጠበቅን ግድ ይላል። የሰዎች ንክኪ የሚበዛባቸው ሱቆችና አገልግሎት ሰጪዎች ተዘግተዋል። በተለይ ደግሞ አስፈላጊነታቸው ይህን ያህል አይደለም የተባሉ ሱቆች መስኮታቸውን ጥርቅም አድርገው ከዘጉ ወራት ሆኗቸዋል።
ኮሮናቫይረስ ዓለምን ሰቅዞ ከያዘ ወዲህ የራቁት ዳንስ ቤት፣ መጠጥ ቤቶችና በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ የሚገኙባቸው ሥፍራዎች በራቸው ከተከረቸመ ውሎ አድሯል።
በወሲብ ንግድ ላይ ያሉ ሰዎች ደንበኞቻችን በአንድ ምሽት ቀለጡ ይላሉ።
ኢስቴል ሉቃስ ሜልበርን ውስጥ ላለፉት 10 ዓመታት ኑሮዋን የገፋችው በወሲብ ንግድ ነው። ነገር ግን ኮቪደ-19 መጥቶ ምድርን ሲያገለባብጣት የእሷ ሥራ አፈር በላ። ለዓመታት የተንከባከበቻቸው ደንበኞቿም ረሷት።
"ለስድስት ወራት ሥራ ሳልሰራ ቆየሁ ማለት ደንበኞቼን አጣሁ ማለት ነው" ትላለች።
ኢስቴል አትዋሽም። ከኮሮናቫይረስ በፊት ገቢዬ ከአማካይ በላይ ነበር ትላለች። ሜልበርን መሃል እሚገኝ አንድ ሠፈር ውስጥ ቤት ሰርታለች። አሁን ግን የገቢዋ ባልቦላ ተቆርጧል። ሥራዋን በኢንተርኔት አማካይነት ለማስቀጠል ብትሞክርም እንደከዚህ በፊቱ ሊሆንላት አልቻለም።
"ደንበኞቼን በኢንተርኔት ላገኛቸው ሞክሬ ነበር። ነገር ግን ሁሉም ሰው ቴክኖሎጂ የገባው ነው ማለት አይቻልም። አንዳንድ ደንበኞቼ ስልካቸውን እንኳን በሥርዓት መጠቀም አይችሉም።''
ምንም እንኳ ምግብ ቤቶችና ካፌዎች መከፈት ቢጀምሩም የወሲብ ንግዱ ግን ገና ፀሐይ አልወጣለትም። አልፎም ሰዎች አካላቸውን ለማነካካት ያላቸው አለመተማመን ደግሞ ሌላው በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሰዎች ፈተና ሆኗል።
"እኔ የተሰማራሁበት ሥራ ከጥቅም ውጪ ሆኖ ልክ መጀመሪያ ስጀምር እንደሆንኩት እንዳልሆን ነው የምፈራው። ሥራው ቢመለስ እንኳ ደንበኞቼ ይኑሩ አይኑሩ አላውቅም። ብቻ ሁሉም ነገር ያስፈራል።"
የአውስትራሊያ መንግሥት በኮቪድ-19 አማካይነት የገቢ ምንጫቸው ለተጓደለባቸው የገንዘብ እርዳታ እያደረገ ነው። ነገር ግን ድጎማው እንዲደርስዎ ከፈገሉ ታክስ የከፈሉበትን ደረሰኝ ማቅረብ ግዴታ ነው። ይህ ደግሞ ሕጋዊ መዝገብ ላይ ስማቸው ላልሰፈረ በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩና ስደተኞች ደንቃራ ነው።
አውስትራሊያ ያሉ በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ብቻ ሳይሆኑ በርካታ አገራት የሚኖሩ የመስኩ ሰዎች ተቸግረዋል። የሌይስተር ዩኒቨርሲቲዋ ቲላ ሳንደርስ፤ መንግሥት ሕጋዊ ወረቀት ላላቸው እንጂ ኢ-መደበኛ ሥራ ለሚሠሩ ድጎማ ሊያደርግ አልፈቀደም ስትል ትሞግታለች።
ችጋር ያንገበገባቸው በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ፤ እንዲሁም የመብት ተሟጋቾች መንግሥታት ኢ-መደበኛ ሥራ ላላቸው ዜጎቻቸው እንዲያስቡ እየሞገቱ ይገኛሉ።
ላስ ቬጋስ ውስጥ የሚገኙ በወሲብ ንግድ ላይ ተሰማሩ ሰዎች 19,300 ዶላር መሰብሰብ ችለዋል። ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ማለት ነው። ጣልያን ውስጥ ደግሞ በወሲብ ንግድ ለሚተዳደሩ የተሰበሰበው ዩሮ 21,700 ደርሷል [820 ሺህ ብር እንደማለት ነው]።
አንዳንዶች ግን ጤናቸውን አደጋ ላይ ጥለው እየሠሩ ነው። አልፎም ከቤታቸው ውጪ ከተያዙ የገንዘብ ቅጣት ሊጣልባቸው ይችላል።
እንግሊዝ ውስጥ ያሉ በርካታ በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሴቶች የልጅ እናት ናቸው ትላለች የመብት ተሟጋቿ ኒኪ አዳምስ።
ይህ የአውሮፓና አሜሪካ እውነታ ነው። እያደጉ ያሉ በሚባሉ አገራት ብዙዎች ኑሯቸውን በወሲብ ንግድ ይገፋሉ። አልፎም ቤተሰብ ያስተዳድራሉ።
ዱዋላቲዳ የተሰኘው ባንግላዴሽ ውስጥ በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ በብዛት የሚኖሩበት መንደር በፖሊስ እየተጠበቁ ነው። መውጣትም ሆነ መግባት ከባድ ሆኗል። መንደሩ በዓለም በወሲብ ንግድ ከሚደራባቸው ሥፍራዎች ትልቁ ተደርጎ ይቆጠራል። በውስጡ ቢያንስ 1300 ሴተኛ አዳሪዎችና 400 ሕፃናት እንደሚኖሩበት ይነገራል።
መንግሥት ይህን መንደር ሲዘጋ የወሲብ ንግድን ገቢ እንደዘጋ አላስተዋለም የሚሉ በርካቶች ናቸው። በርካቶች ከዚያም ከዚህም በሚያገኙት እርዳታ ነው ኑሯቸውን እየገፉ ያሉት።
ትክክለኛ ስሟን ማሳወቅ ያልፈለግችው የሦስት ልጆች እናቷ ናዝማ የምንበላው የለንም፤ ሥራም የለንም ምን እንደሚውጠን አላውቅም ትላለች። ''ምንም እንኳ መሥራት ብፈልግም ቫይረሱ ቢይዘኝስ የሚለው ጭንቀት ሊገለኝ ነው።''
በዓለም ደረጃ የወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ትልቁ ፈተና የጤና ኢንሹራንስ አለመኖር ነው። በተለይ ደግሞ ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች የጤና ኢንሹራንስ ከሌላቸው ፈተናው ይልቃል።
የዘመኑ ፈተና በወሲብ ንግድ ላይ በተሰማሩት ሰዎች ላይ ይበልጥ እንዲከብድ የሚያደርገው ንግዱ ለማንሰራራት ገና ብዙ ይቀረዋል መባሉ ነው። ወረርሽኙ ተረጋግቶ ሰዎች ወደ ቀድሞ ኑሯቸው ቢመለሱ እንኳ እምነት ላይኖራቸው ስለሚችል ሴተኛ አዳሪዎችን ላይጎበኙ ይችላሉ።














