ስለ ወሲብ እንዲያስቡ የማይፈቀድላቸው የኢራን ተቃዋሚዎ ቡድን አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢራን መንግሥት ዋነኛ ተቃዋሚ ቡድን የሆነው ሙጃሂዲን-ኢ-ኻልቅ አባላት ለስድስት ዓመታት መቀመጫቸው አልባኒያ አድርገው ቆይተዋል። ነገር ግን በርካታ አባላት በየቀኑ ቡድኑን ጥለው ይኮበልላሉ። ምክንያታቸው ደግሞ የቡድኑ ሕግ እጅግ ጠበቅ ያለ መሆኑ ነው።
ቡድኑ፤ አባላቱ ከወሲብ እንዲቆጠቡ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነትም የተገደበ እንዲሆን ያስገድዳል። ይህንን ቡድን ለመቀላቀል ወደ አልባኒያ ዋና ከተማ ቲራና ቢመጡም ያላሰቡት ገጥሟቸዋል።
«ከባለቤቴና ከልጄ ጋር ካወራሁ 37 ዓመታት አለፈኝ። የሞትኩ መስሏቸው ነበር። 'ኧረ አለሁ፤ አልባኒያ እየኖርኩ ነው' ስላቸው አለቀሱ።»
ከበርካታ ዓመታት በኋላ ቤተሰቦቹን በስልክ ያገኘው የ60 ዓመቱ ጎላም ሚራዚ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር ቡድኑን ጥሎ የሸሸው። አሁን ቲራና ውስጥ ከተቃዋሚም ከመንግሥትም ጎራ ሳይሆን ይኖራል። የተቃዋሚው ቡድን አባላት ግን ለኢራን መንግሥት እየሰለለ ነው ሲሉ ይጠረጥሩታል።
ኤምኢኬ በሚል ቅጥያ የሚታወቀው ይህ ተቃዋሚ ቡድን እጅግ የከፋ ታሪክ ያለው ነው። እስላማዊ ማርክሲስት የነበረው ቡድን የ1979 [በግሪጎሪ አቆጣጠር] የኢራን አብዮትን ደግፎ ከአያቶላህ ኮሚኒ ጋር ቢያብርም የኋላ ኋላ ቁርሾ መፈጠሩ አልቀረም። የዛኔ ነው የቡድኑ አባላት ሕይወታቸውን ለማቆየት ሽሽት የጀመሩት።
ጎላም ሚራዚ የኢራን ጦር ሠራዊት አባል ነበር። በኢራን - ኢራቅ ጦርነት ወቅት በሳዳም ሁሴን ወታደሮች ተይዞ ኢራቅ ውስጥ ለ8 ዓመታት በእሥር ከረመ። ከዚያ ሲወጣ ነው የተቃዋሚውን ጎራ የተቀላቀለው።
ኤምኢኬ መሸሸጊያውን አልባኒያ ካደረገ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላት ኮብልለዋል። አንዳንዶቹ ለሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ገንዘብ ሰጥተው ወደ ሌሎች የአውⶂጳ ሃገራት ተሰደዋል። ሚራዚን ጨምሮ በርካቶች ግን አሁንም አልባኒያ ይኖራሉ። ሃገር የላቸውም፤ ሥራም ማግኘት አይችሉም።
ከኢራቅ ወደ አልባኒያ
ኤምኢኬ በአውሮጳ እና በዩናይትድ ስቴትስ አሸባሪ ቡድን ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ሳዳም ሁሴን የቡድኑ ቀንደኛ ደጋፊና አቃፊ ነበሩ። ሳዳም ሁሴን ሲገደሉ ግን ቡድኑ ብቻውን ቀረ። አባላቱን እያሳደዱ የሚያጠቁም በዙ።
ይሄኔ ነው የአሜሪካ መንግሥት 3 ሺህ ገደማ የኤምኢኬ አባላትን ከአልባኒያ መንግሥት ጋር በተደረገ ስምምነት ወደ ቲራና ያጋዘው። ይህ የሆነው ከስድስት ዓመታት በፊት ነው።

ለሚራዚና ጓደኞቹ ሕይወት አልባኒያ ውስጥ ለየት ያለ ነበር። ሚራዚ አልባኒያ ውስጥ ታዳጊዎች እንኳ ሳይቀር የእጅ ስልክ ይዘው ሲመለከት መገረሙ አልቀረም። የቡድኑ አባላት እንደልባቸው መውጣት መግባት ጀመሩ። አንፃራዊ ነፃነት ያጣጥሙም ጀመር።
ሌላኛው የቡድኑ አባል የነበረው ሃሳን ሄይራኒ ከሚኖሩበት ሕንፃ ጓሮ ስፖርት እንድንሠራ አለቆቻችን ያዙን ነበር ሲል ያወሳል። ሄይራኒ እና ጓደኞቹ ግን ተደብቀው በመውጣት 'ኢንተርኔት ካፌዎችን' ይጎበኛሉ። ቤተሰቦቻቸውንም ያናግራሉ።
ከሁለት ዓመት በፊት ግን ኤምኢኬ የአድራሻ ለውጥ አደረገ። ከዋና ከተማዋ 30 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ ከሚገኝ ሥፍራ ላይ ዋና መናኸሪያውን አደረገ። በብረት አጥር ወደ ተሸበበው አዲስ ሕንፃ ለመግባት ፈቃድ ማግኘት ግድ ይላል።
ባለፈው ሐምሌ ኤምኢኬ 'ኢራንን ነፃ ትውጣ' የተሰኘ ዝግጅት አዘጋጅቶ በርካቶች ተገኝተው ነበር። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጠበቃ ሩዲ ጉሊያኒም እንግዳ ነበሩ። የቡድኑ ማኒፌስቶ በኢራን ሰበዓዊ መብት እንዲከበር፤ የፆታ እኩልነት እንዲሰፍንና አሳታፊ ዴሞክራሲ እንዲሰራፋ ያትታል።
ሃሰን ሄይራኒ ግን ምኑም አይዋጥለትም። ቡድኑን ጥዬ የኮበለልኩት አመራሮቻችን ጨቋኝ ስለሆኑ ነው ይላል፤ በተለይ ደግሞ የግል ሕይወትን በተመለከተ ይላል በ20ዎቹ ዕድሜው ላይ ሳለ ቡድኑን የተቀላቀለው ሄይራኒ።
«አንዲት ማስታወሻ ደብተር ነበረችን። ወሲብን የተመለከተ ምንም ዓይነት ነገር ቢያጋጥመን እንድንፅፈበት ተብሎ የተሰጠን። ለምሳሌ 'ዛሬ ጥዋት ብልቴ ቆሞ ነበር' ብለን እንፅፋለን።»
ኤምኢኬ የፍቅር ግንኙነትና ትዳር አይፈቅድም። በቀደመው ጊዜ ግን እንዲህ አልነበረም። ባለትዳሮች ልጆቻቸውን ይዘው ይቀላቀሉም ነበር። ነገር ግን ከኢራን ወታደሮች ጋር በነበር ውጊያ ኤምኢኪ መሸነፉን ተከትሎ ሕግ እንዲጠብቅ ሆነ። በፍቅር ግንኙነቶች ምክንያት መዘነጋት መጥቷል ያሉ አዛዦች ነገሩን አከረሩት። ትዳሮች ፈረሱ፤ ሕፃናት ወደ መጡበት ተላኩ።
ማስታወሻ ደብተሯ ላይ ግላዊ ሕልሞቻቸውን ሳይቀር መፃፍ ግዴታ ነው። «ለምሳሌ ቴሌቪዥን ላይ ሕፃናት አይቼ 'አኔም ልጆች በኖሩኝ ብዬ ተመኘሁ' ብለን እንፅፍ ነበር» ይላል ሄይራኒ።
በየቀኑ ስብሰባ ይካሄዳል፤ ወታደሮቹም የፃፉትን በአዛዦቻቸው ፊት ማንበብ አለባቸው። ሄይራኒ ሸሽቶ የመጣውን የካምፕ ኑሮው ከጆርጅ ኦርዌል መፅሐፍ ጋር ያመሳስለዋል፤ 'አኒማል ፋርም' ወይም የእንስሳት ገበያ።
ቢቢሲ ኤምኢኬን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ቡድኑ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት አልተሳካም።
ቲራና የሚኖሩት ሙጃሂዲኖችን ለመግደል የኢራን መንግሥት ለመግደል እያሤረ ነው ሲል የአውሮጳ ሕብረት ይኮንናል። በአልባኒያ የኢራን ኤምባሲ ስለጉዳዩ ለቢቢሲ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ሚራዚም ብቻ ሳይሆን ሄይራኒም ለኢራን መንግሥት ይሰልላል ተብሎ ይጠረጠራል። ሁለቱም ክሱን ያስተባብላሉ። ሁለቱም አልባኒያ ውስጥ ኑሯቸውን መሥርተው ይኖራሉ። የ40 ዓመቱ ሄይራኒ አንዲት አልባኒያዊት የፍቅር ጓደኛ አለችው።
ጎላም ግን ጤና ይጎለዋል። ከቤተሰቡ መለየቱ ሁሌም ያንገበግበዋል። ገና በጨቅላነቱ ጥሎት የሄደው ልጁ አሁን 40 ዓመት ሆኖታል። በዋትስአፕ ቢነጋገሩም መቼም በአካል እንደመገናኘት አይሆንም። የኢራን ኤምባሲ ሄዶ ለእርዳታ እጁን ዘርግቷል። ኢራን የሚገኙት ቤተሰቦቹም መጥተው መጠየቅ እንዲቻላቸው አሳስበዋል። ሰሚ ጆሮ ያገኙ ግን አይመስልም። ሚራዚ ግን ተስፋ ያደርጋል። ዜግነት አልባ ቢሆንም፤ ፓስፖርት ባይኖረውም ሕልሙን ግን አልተነሳም።













